መቅድም

ከአድዋ ድል በኋላ አጼ ምኒልክ ባገር ውስጥም ሆነ ካገር ውጭ ከፍተኛ ክብርና ሞገስን ተቀዳጁ። የኢትዮጵያን ግዛት ከመቼውም በበለጠ ሁኔታ ከማስፋታቸውም በላይ፣ በኢጣሊያ ጦር ላይ የተቀዳጁት ድል በኃያላን መንግሥታት ዘንድ ከበሬታን አስገኘላቸው። በተገኘውም አንፃራዊ ሰላም ተጠቅመው ላገራቸው ይመኙላት የነበረውን የአውሮጳ ሥልጣኔ በከፊል ማስፋፋት ጀመሩ። ከነዚህም የእድገት ምልክቶች ጎላ ብለው የሚታዩት የምድር ባቡር፣ ባንክና ትምህርት ቤት ነበሩ።
ይሁን እንጂ ይህን የዘመናዊ ሥልጣኔ አውታሮችን ተግባር ገና እንደ ተያያዙት ጤናቸው በመታወኩ ሊገፉበት አልቻሉም። ይልቁንም እሳቸው እየተዳከሙ ሲሄዱ፣ ዙሪያቸው ባሉት መሣፍንትና መኳንንት መካከል፣ ባለቤታቸውን እቴጌ ጣይቱን ጨምሮ፣ አያሌ ዓመታት የፈጀ የሥልጣን ሽኩቻ ተጀመረ። ይህ ሽኩቻ እልባት ያገኘው ራስ (ኋላ ንጉሥ) ተፈሪ በ1923 ዓ.ም. ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተብለው የንጉሠ ነገሥትነትን ዘውድ ሲጭኑ ነው። ስለሆነም አያሌ የታሪክ መጻሕፍት ትኩረታቸውን ያሳረፉት ወይ ባጼ ምኒልክ ወይ በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ላይ ነው።
ይህ ሠላሳ ዓመት ያህል የፈጀና የፖለቲካ ውዝግብ የመላበት የታሪክ ዘመን ለረጅም ጊዜ ብዙ ትኩረት ሳያገኝ ቀርቶ ነበር። ለዚህም አንዱ ምክንያት፣ በውጭ አገር ሰዎች ከሚጻፈውና ከሚዘገበው ባሻገር አገራዊ የታሪክ ምንጮች እምብዛም ባለመገኘታቸው ነው። ለአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ዋነኛ ዋቢ መጽሐፍ ሆኖ ሲያገለግል የቈየው በጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ የተጻፈው ዜና መዋዕላቸውም የሚያቆመው ሕመማቸው እየበረታባቸው የመጣው ዳግማዊ ምኒልክ በ1901 ዓ.ም. የልጅ ልጃቸውን ኢያሱ ሚካኤልን አልጋ ወራሽ ብለው ሰይመው ዓዋጅ ሲያስነግሩ ነው።
አሁን ለኅትመት የበቃው በብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ የተጻፈው “የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ካየሁትና ከሰማሁት” “የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በአቤቶ ኢያሱ ዘመነ መንግሥት ካየሁትና ከሰማሁት” “የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥት ካየሁትና ከሰማሁት” በሚል አርዕስት በሦስት ቅጽ ያዘጋጁት መጽሐፍ ይህን ክፍተት ባጥጋቢ ሁኔታ የሚሞላው በመሆኑ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነው። የመጽሐፉ የጊዜ አድማስ ከ1896 እስከ 1922 ዓ.ም. ሲሆን፣ በየዓመቱ የነበሩት ድርጊቶችና ክንዋኔዎች በሚያስደንቅ ምልኣትና ጥንቃቄ ተዘግበው ይገኛሉ። ይህ ታሪኩን በዓመተ ምሕረት እየፈረጁ የማቅረብ ስልት በተወሰኑ ዓመታት የተደረጉትን ወይም የተከናወኑትን ታሪካዊ ክስተቶች ማወቅ ለሚሻ የታሪክ ተመራማሪ አመቺነቱ ከመጽሐፉ አያሌ ጠቃሚ ገፅታዎች አንዱ ነው። በሌላ አነጋገር መጽሐፉ እንደ አንድ ወጥ ታሪክም፣ እንደ ማጣቀሻ (ሬፈረንስ) ሥራም ሊያገለግል ይችላል ማለት ነው።
ከፍ ሲል የብላታ አተራረክ ምን ያህል ጥንቃቄ የተሞላበት እንደ ሆነ ገልጬ ነበር። ይህን አባባሌን በሁለት ማስረጃዎች መደገፍ እፈልጋለሁ። አንደኛው ቀኖችና ዓመተ ምሕረት በሚጠቅሱበት ጊዜ ይህ ነው የሚባል ዝንፈት አለመታየቱ ነው። ይህ በኢትዮጵያ የዘመን አቈጣጠር ለሚጠቀሱት ብቻ ሳይሆን በአውሮፓ አቈጣጠርም ለሚዘገቡት ነው። ሌላው ለዚሁ ጥንቃቄ በማስረጃነት ሊቀርብ የሚችለው ደራሲው በሰገሌ ጦርነት ላይ የሞቱትን የጦር መሪዎች ሲያትቱ፣ በሸዋ በኩል የሞቱትን ከዘረዘሩ በኋላ፤ “በወሎም በኩል የሞቱትን የታላላቅ ሰዎች ስም ለመጻፍ ፈልጌ ነበር፣ ነገር ግን አረጋግጦ የሚነግረኝ ስላጣሁ ልጽፈው አልቻልሁም” ብለው አልፈዋል። (ገጽ 176) ከዚያም አልፎ ደራሲው በየቦታው ይህንን የሰማሁት ከእገሌ ነው እያሉ ዋቢያቸውን በመጥቀስ የታሪኩን ሥረ-መሠረት ያጋሩናል።
ሌላው የመጽሐፉ አደረጃጀት ጠቃሚ ገፅታ፣ ደራሲው በየዓመቱ ከነበሩት ዋና ዋና ክንዋኔዎችና ድርጊቶች ባሻገር የታሪኩ እምብርት ባይሆኑም ከተለያየ አንፃር ታሪካዊ ጠቀሜ ያላቸውን ሁኔታዎች ባጭር ባጭሩ መተረካቸው ነው። ለዚህም ደራሲው የመረጡት ስልት በየምዕራፉ መጨረሻ ላይ “ስለ ልዩ ልዩ ነገር” የሚል አንቀጽ መጨመራቸው ነው። በዚህ ርዕስ ከተካተቱት ሁኔታዎች መካከል የመሬት መንቀጥቀጥ (ገጽ 35)፣ የፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዝነኛ ፍርዶች (ገጽ 51)፣ የሃይማኖት ክርክሮች (ገጽ 100) እና አውቶሞቢል በአዲስ አበባ እየተበራከተ መምጣት (ገጽ 272) ይገኙበታል።
እንደዚሁም በየምዕራፉ ማሳረጊያ ላይ የቀረቡት ቀንና ዓመተ ምሕረት ተሟልተው የሚገኙባቸው “ስለ መኳንንት ዜና ሞት” የተሰኙት አንቀጾች ለታሪክ ምርምር ልዩ ጠቀሜ አላቸው። አሁን ልጃቸው አቶ አምኃ መጽሐፉን በሚያሳትምበት ጊዜ ብላታ በሌላ ጊዜ የጻፉትን “አስማተ ሙታን” የተሰኘውን ሰነድ በአባሪነት ማቅረቡ ይህን ጠቀሜታ የጎላ ያደርገዋል። ሌላው ከዚህ ጋር የሚጠቀሰው ነገር፣ ብዙውን ጊዜ ደራሲው በዘመኑ የሞቱትን መኳንንት ስም ከመጥቀስ አልፈው፣ መለስ ብለው የሟቹን የሕይወት ታሪክ (ከልደት እስከ ሞት) በዝርዝር የሚቃኙበት ሁኔታ ነው። እንዲህ ሕይወታቸው ከሚቃኘው መኳንንት መካከል የወሎው ንጉሥ ሚካኤል ይገኙበታል (ገጽ 223-226)። ይህ ቅኝት ከልደታቸው አንሥቶ፣ የፖለቲካ ሕይወታቸውን ዐበይት ምዕራፎችና የትውልድ ሐረጋቸውን ጨምሮ፣ የሰባት ልጆቻቸውን የስም ዝርዝርና ያንዳንዱንም የልደት ዘመን ያካትታል።
መጽሐፉ ይህን ከላይ የተዘረዘረውን ዓይነት ለታሪክ ምርምር ጠቃሚ የሆነ አቀራረብ ሲኖረው፤ ብልቱ ግን ይዘቱ ላይ ነው። እዚህ ላይ ብዙ ማለት ቢቻልም፤ በዚህ መቅድም ግን ማውሳት የሚቻለው ዋና ዋናዎቹን ነው። የመጽሐፉ ዐቢይ ታሪካዊ ፋይዳ ስለ አቤቶ ኢያሱና በተለይም ስለ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥት የተሟላ ሥዕል መስጠቱ ላይ ሲሆን፤ ስለ ዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥትም አያሌ ጠቃሚ መረጃዎችን ያዘለ ነው። ከነዚህም መካከል ሊጠቀሱ የሚችሉት፣ ስለ ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት (ብላታ “የቋንቋ ተማሪ ቤት” ይሉታል) መቋቋም፣ የእቴጌ ጣይቱ ሥልጣን መግነንና ያስከተለው ዓመፅ፣ የዓመፁ ሞተር የነበረው የመሃል ሰፋሪ ጦር ሚና ነው።
በኔ ግምት፣ በታሪኩ ውስጥ አምስት ጊዜ መድረክ ላይ ብቅ በማለት በዘመኑ የፖለቲካ ሹም ሽር ወሳኝ ሚና የተጫወተውን የዚህን ሠራዊት ምንነትና እንቅስቃሴዎቹን እንደ ብላታ ትዝታዎች አጉልቶ ለማውጣት የቻለ መጽሐፍ ያለ አይመስለኝም። በብላታ አገላለፅ አድማ “መቋጠር”ን ሥራዬ ብሎ የተያያዘው ከቤተ መንግሥቱ ጋር በቅርብ የተሳሰረ ይህ ሠራዊት በ1902 እቴጌ ጣይቱን ከሥልጣን ገሸሽ በማስደረግ፣ በ1909 ልጅ ኢያሱን ከዙፋን በማውረድ፣ በ1910 ሚኒስትሮችን በማሻርና በ1921 ራስ ተፈሪን ንጉሥ በማሰኘት ወሳኝ የፖለቲካ ሚና ተጫውቷል።
የልጅ ኢያሱ ዘመነ መንግሥት አንድም በመረጃ አቅርቦት ማነስ የተነሣ፣ አሊያም ያሉት መረጃዎች የተዛቡ በመሆናቸው በቅጡ ሊታወቅ ሳይችል ረጅም ዘመናት አሳልፏል። ወጣቱ መሪ የሚታወቁትም ዝቅ ሲል በሴሰኝነት፣ ከፍ ሲል ደግሞ በመናፍቅነት ሆኖ ቈይቷል። እያደር ግን፣ አዳዲስ መረጃዎች ብቅ በማለታቸው የዚያ አወዛጋቢ ዘመን ገፅ እየተሟላና እየተስተካከለ ሊመጣ ችሏል። ለዚህ ትልቅ አስተዋፅኦ ለማድረግ ከቻሉት ሰነዶች መካከል አሁን የታተመው የብላታ መርስዔ ኀዘን ትዝታዎች ናቸው። ብላታ ወጣቱ ንጉሥ የአስተዳደር ደንቦችን ለማሻሻል ያደረጉትን ጥረት ከማሳየት አልፈው፤ በስፋት የታሙበትንና ከዙፋን ለመውረዳቸው ዋነኛ ሰበብ የሆነውን የመስለም ጒዳይ እምብዛም እንዳልተቀበሉት “በሃይማኖትና በባህል ረገድ ግድ የለሽ መሆናቸው መሣሪያ ሆኖ ለሕዝብ እንደ ቀረበና ወደፊትም የብዙዎችን ሕይወት አስጠፍቶ ሥራውን ሲሠራ እንመለከታለን” የሚለው አቀራረባቸው በግልፅ ያሳያል (ስርዝ የራሴ)።
ብላታ ምንም እንኳን ብዙ ሕይወት የጠፋበትን የሰገሌን ጦርነት በዝርዝር ለመጻፍ ፍላጎቱ ባይኖራቸውም፣ የርስ በርስን ጦርነት አስከፊነት ለማሳየት ካለው ጠቀሜ በመነሳት ብቻ ያንን ዐቢይ ታሪካዊ ክንዋኔ በስፋትና በጥንቃቄ ተርከውልናል። ከዚያም በመቀጠል የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱን ሥርዓተ ንግሥ እንደ ሲኒማ ቍልጭ ብሎ የቀረበበት መጽሐፍ በመሆኑ ምናልባትም እኔ እስከማውቀው በዚህ ረገድ ብቸኛው የታሪክ ሰነድ ነው ማለት ይቻላል። እስካሁን በብዛት ሲወሳ ለቈየው ራስ ተፈሪ መጀመሪያ የንጉሥነት፣ ከሁለት ዓመት በኋላም የንጉሠ ነገሥትነት ዘውድ ለጫኑበት ሥርዓትም እንደ መቅድም የሚያገለግል ነው።
ዘውዲቱ ንግሥተ ነገሥታት ይባሉ እንጂ የድኅረ-ኢያሱ የፖለቲካ ሥርዓት በታሪክ የሚታወቀው የራስ ተፈሪ ሥልጣን ቀስ በቀስ እየገነነ በመምጣቱ ነው። በዚህም ረገድ የብላታ መርስዔ ኀዘን መጽሐፍ አያሌ ዝርዝር መረጃዎችን ያካፍለናል። የራስ ተፈሪን ሥልጣን እያጎለበቱ ከሄዱት ክስተቶች መካከል የሚከተሉት ዐቢይ ስፍራ የያዙ ነበሩ፡- ኢትዮጵያን ወደ ዓለም ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) ማስገባት፣ በአውሮጳ አገራት በ1916 ያደረጉት ጒብኝት፣ የደጃዝማች ባልቻና የደጃዝማች አባ ውቃው መውደቅና በመጨረሻም የንግሥቲቱ ባለቤት የነበሩት ራስ ጉግሣ በአንቺም ጦርነት መረታትና መሞት። እነዚህ ክስተቶች ሁሉ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በዝርዝር፣ አንዳንዴም በታሪካዊ ሰነዶች አባሪነት ተብራርተው ይገኛሉ።
ከፖለቲካው ባሻገርም ባገሪቱ ማኅበራዊ ሕይወት ላይ ትልቅ አሻራ ትተው ያለፉ ክስተቶች ተዘርዝረው መገኘታቸው የመጽሐፉን ጠቀሜ ያጎላዋል። ከነዚህም መካከል ለብዙ ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት የነበረው በ1911 የተከሰተው የኅዳር በሽታ ልዩ ግምት የሚሰጠው ነው። ሌሎች እንዲሁ በስፋት ከተተረኩት ሁኔታዎች መካከል፣ በ1921 ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት ለመጀመርያ ጊዜ መሾም፣ በዚሁ ዓመተ ምሕረት የመጀመሪያው አውሮፕላን መምጣትና በ1922 የለገሀር ሕንፃና የይሁዳ አንበሳ ሐውልት ምረቃ በዓል ይገኙበታል።
ባጠቃላይ፣ እነሆ ባንድ ቅፅ ተጠቃለው ለኅትመት የበቁት የብላታ መርስዔ ኀዘን ትዝታዎች የሀገራችንን የሐያኛው መቶ ዓመት መጀመርያ ዐሠርት ዓመታት በዝርዝር ለማወቅ ለሚሻ አንባቢ ትልቅ የታሪክ ድግስ ይዘው ቀርበዋል። ለታሪክ ተማሪዎችና ተመራማሪዎችም ካጠገባቸው ሊለይ የማይችል የሰነድ ስንቅ ነው።
ባሕሩ ዘውዴ