ማስተዋወቂያ

የብላታ መርስዔ ኀዘን የወሰን አካላይነት ታሪክ
– ፩ –
ለእኔ ትውልድ ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ አዲስ ሰው አይደሉም። ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በነበርንበት ጊዜ «የአማርኛ ሰዋስው» የሚለው መጽሐፋቸው መማሪያችን ስለነበረ ከስማቸው ጋር በደንብ እንተዋወቃለን፤ በኋላ በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በማስተምርበት ጊዜ ደግሞ እኔም በተራዬ አንድ የኢትዮጵያ ካርታዎች ስብስብ (አትላስ) ለመማርያ አሳትሜ ስለነበረ ለትምህርት ሚኒስትሩ ለአቶ አካለ ወርቅ ሀብተ ወልድ ለመስጠት ወደ ቢሮአቸው ስገባ ብላታ መርስዔ ኀዘን ነበሩ፤ አትላሱን ትኩር ብለው እያዩ ሲያገላብጡ ቆዩና «ጅሩ የት አለ?» ብለው ሲጠይቁኝ በዚያ የካርታ መስፈርት እንደ ጅሩ ያለ ትንሽ ቦታ አይገባም ስላቸው፣ «አዬ! ታዲያ ጅሩ የሌለበት ካርታ ሠርተህ ነው የኢትዮጵያ የምትለው!» ብለው ቀለዱብኝ፤ ይህ የመጀመሪያም፣ የመጨረሻም ግንኙነታችን ነበር፤ ግንኙነታችን መቀጠል ነበረበት፤ ግንኙነታችን ያልቀጠለው በእኔ አለማወቅና በእሳቸው አለመናገር ነው፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ወደ ሃምሳ ዓመታት ይጠጋል።
ብላታ መርስዔ ኀዘን በካርታ እየተጠቀሙ የሠሩ መሆናቸውን እሳቸው ያን ጊዜ አልነገሩኝም፤ እኔም ብጠየቅ እሳቸው ስለ ካርታ አያውቁም ብዬ በመሐላ እናገር ነበር፤ ለምን ካርታውን ሲመለከቱ በድንበር ክልል ተሰማርተው እንደነበረ አልነገሩኝም? ዛሬ ሳይጠየቅ የማያውቀውን ለመናገር የሚሽቀዳደም ትውልድ በበቀለበት ዘመን በብላታ አስተዳደግ የሚያውቁትንና የሠሩበትንም ቢሆን ሳይጠየቁ መናገር ነውር ሆኖ ይታይ እንደነበረ መገመቱ በመሀከላችን ያለውን የባህል ርቀት የሚያመለክት ይመስለኛል፤ ስለዚህም ያልተናገሩበት አንዱ ምክንያት የባህል ተጽእኖ ሊሆን ይችላል፤ ሌላው ደግሞ ዐዋቂ አንድ ብቻ በሆነበት አገር ዐውቆ መገኘትና የሚያውቁትን ሳይጠየቁ መናገር ሊያጋልጥና ሊያስቆጣ የሚያስችል መሆኑ ነው፤ ይህን ሐሳብ በሌላ ምሳሌ ላስረዳ፤ ደጃዝማች የማነ ሐሰን አርበኛ ነበሩ፤ ስለ አርበኝነታቸው ዘመን ሲናገሩ የሰዎችን ስም፣ የወንዙን፣ የጋራውንና የሸንተረሩን ስም እየጠሩ ነበር፤ ብዙ ጊዜ በተመስጦ አዳምጫቸዋለሁ፤ ስለዚህም አንድ ቀን «እባክዎን በተመቸዎ ቀንና ሰዓት ለዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪዎች ንግግር ያድርጉልን» ብዬ ስጠይቃቸው መልሳቸው «ምነው መስፍን ወዳጅ መስለኸኝ! ምን በደልኩህ? በል ተወኝ፤ በቃኝ ያንተ ነገር» ነበር፤ ገባኝ፤ የብዙ ታላላቅ ሰዎች ታሪክ ተዳፍኖ የቀረው እንደዚህ ነው፤ ታሪካችንን ለመማር ፈረንጅ አገር የምንሄደው ለዚህ ነው፤ እውነት ይሁንም አይሁንም የፈረንጅ ምስክር የምንፈልገው ለዚህ ነው።
በተጨማሪም ብላታ በጅጅጋ የትምህርት ቤት ዲሬክተር ሆነው ሲሠሩ እንደነበረ ያሁኑ መጽሐፋቸው ይነግረናል፤ ስለዚህም ለኦጋዴን እንግዳ አልነበሩም ማለት ነው፤ ከዚያም በላይ ዋናው ነገር ለካ ገና እኔ በተወለድሁበት ዓመት በኢትዮጵያና በብሪታንያ ሶማሊላንድ ወሰን በመካለሉ ሥራ ተሳትፈዋል! ለካ ስለ ካርታ ያውቃሉ! ግን የእኔን ካርታዎች ሲያዩ ትዝታ ተቀስቅሶባቸው የተነፈሱት ቃል አልነበረም።
ብላታ መርስዔ ኀዘን ስለ ካርታና ስለ ድንበር መካለል ያላቸውን ዕውቀት ምሥጢር ያደረጉብኝን ምክንያት መግለጹ ብቻ አይበቃኝም፣ እኔም በግል ተጎድቻለሁ፤ በዚያው ዘመን እኔ በኢትዮጵያና በብሪታንያ ሶማሊላንድ፣ በኢትዮጵያና በኢጣልያ ሶማልያ መካከል የነበረውን ውዝግብ በማጥናት ላይ ነበርሁ፤ ስለዚህም በጥያቄዎች ቀስቅሼ ከብላታ ከማገኘው መልስ ጋር በዚህ መጽሐፍ የተገለጹት መረጃዎች በጣም ይረዱኝ ነበር፤ ያንን ዕድል ሳላገኝ ቀርቻለሁ።
– ፪ –
የኢትዮጵያ ሀገረ–መንግሥት ለብዙ ምዕተ–ዓመታት የተከለለ ድንበር አልነበረውም፤ እንደየነገሥታቱ ፈቃድና ብርታት የሚለዋወጥ ነበር፤ ቢሆንም ኢትዮጵያ ከአውሮጳውያን ጋር የአፍሪካ ቅርጫ ተካፋይ አልነበረችም፤ ኢትዮጵያ (ኢትዮጵያ ስል ዛሬ ባዕድ የሆነችውን ኤርትራንም ጨምሬ ነው) በዜጎችዋ መስዋዕትነት ነፃነትዋን ጠብቃ መኖርዋ ብቻ ከአፍሪካ አገሮች የተለየች ያደርጋታል፤ እውነቱ እንዲህ ነው፡- አውሮጳውያን አፍሪካን በሚሻሙበት ዘመን መጨረሻ ላይ ኢትዮጵያ ላይ የሦስቱም የአውሮጳ ኃያላን (በዚያን ጊዜ የዓለም ኃያላን) ሌላውን ሁሉ ጨርሰው በኢትዮጵያ ላይ አሰፈሰፉ፤ ኢትዮጵያን ለመቀራመትም የተለያዩ ስምምነቶችን ተዋዋሉ፤ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች የተጠቀሙበትን የማታለልና የማስፈራራት ዘዴ ሁሉ ሲጨርሱ በጦርነት ለማስገበር ኢጣልያ ተሽቀዳድማ እየገፋች ወደ ኢትዮጵያ ዘልቃ የአድዋ ጦርነት ሆነ፤ የአድዋ ጦርነት የኢትዮጵያን ሀገረ–መንግሥት የአውሮጳ ኃያላን መንግሥታት እንደ እኩያቸው አድርገው እንዲቀበሉ አስገደዳቸው፤ ይህን ነው የማያውቁ ዐዋቂ ነን ባዮች በአፍሪካ ቅርጫ ተካፋይ መሆን የሚያደርጉት።
በአድዋ ድል ማግሥት ከኢትዮጵያ ጋር ድንበርተኞች የሆኑ ግዛቶች ያላቸው የአውሮጳ አገሮች ሁሉ ከኢትዮጵያ ጋር ሕጋዊ የወሰን ውሎችን የመፈጸም እሽቅድምድም ያዙ፤ ከብሪታንያም ጋር ሆነ ከፈረንሳይ፣ ወይም ከኢጣልያ ጋር የተደረጉት ሁነኛ የወሰን ውሎች ሁሉ ከአድዋ ድል በኋላ ነው፤ የአውሮጳ ቄሣራውያን ኢትዮጵያን ከመክበባቸው በፊት ኢትዮጵያን ሊቀናቀን የሚችል ሌላ ኃይል በአካባቢው አልነበረም ስለዚህም የወሰን ጥያቄ የሚነሣበት ምክንያት አልነበረም።
የአውሮጳ ቄሣራውያን ኃይሎች ኢትዮጵያን ዙሪያዋን ከከበቡ በኋላ በወሰን ድርድሩ ላይ የነበረውን የኃይል ሚዛን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፤ ወደ ዝርዝር ሳንገባ የብሪታንያ ሶማሊላንድ ድንበር ከሐረርና ከድሬዳዋ እንዲርቅ ወደ ምሥራቅ ተገፍቶአል፤ የብሪታንያ ሶማሊላንድ በአንድ በኩል የፈረንሳይ ሶማሊላንድ ይባል ከነበረው ጋር፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከኢጣልያ ሶማልያ ጋር የሚዋሰን መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፤ የብሪታንያ ሶማሊላንድና የኢትዮጵያ ወሰን የራስ መኰንንንና የአማካሪዎቻቸውን ብልህነት ያሳያል፤ በሱዳን በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ድንበር ከዓባይና ከቅርንጫፎቹ እንዲርቅ ወደ ምሥራቅ ተገፍቶአል፤ ይህ ብሪታንያ ለግዛቶችዋ ለግብጽና ለሱዳን ስትል ያሳየችውን ግፊት ሲያመለክት ኢጣልያ ከኢትዮጵያ ምንም ያህል የማትሻል እንደነበረች ያመለክታል።
በኢትዮጵያና በብሪታንያ ሶማሊላንድ መካከል ያለው የወሰን ውል የተፈጸመው ራስ መኰንን የአጼ ምኒልክ ወኪል ሆነው፣ ሚስተር ሬነል ሮድ ደግሞ የንግሥት ቪክቶሪያ ወኪል ሆነው ባደረጉት የደብዳቤ ልውውጥ ነው፤ የደብዳቤ ልውውጦቹ የተደረጉት እ.አ.አ. ከጁላይ 1897 እስከ ዲሴምበር 1897 ነበር፤ የእነዚህን ሰነዶች ቅጂ በአማርኛ አላገኘሁም።
– ፫ –
የኢጣልያ ሶማልያም፣ የብሪታንያ ሶማሊላንድም ነፃነታቸውን አገኙና ገና ለየብቻቸው ሳያጣጥሙትና በጥልቀት ሳያስቡበት በስሜት ፈንድቀው ተዋሃዱ፤ ሶማልያውያን የረገጡት መሬት ሁሉ የሶማሌዎች መሆን አለበት ብለው ለጦርነት ይዘጋጁ ጀመር፤ በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ሁለቴ ጦርነት አነሡ፤ በዚህ ጊዜ እኔ የኢትዮጵያንና የሶማልያን ድንበር ማጥናት ጀመርሁ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ለጥናቱ በውል የሚረዳኝ ሰውም ሆነ ሰነድ አላገኘሁም፤ በሙሉ በእንግሊዞችና በኢጣልያኖች የተጻፉ መጽሐፎችና ሰነዶች መጠቀም ተገደድሁ፤ ለማናቸውም ጽሑፌን መጀመሪያ በሎንዶን አሳተምሁና በኢትዮጵያም እንዲታተም ስለፈለግሁ ሙከራው ጣጣ ፈጠረ፤ በመጨረሻም የማስታወቂያ ሚኒስትር ወደነበረው ሥዩም ሐረጎት ድረስ ሄጄ እንዲታተም ማስፈቀድ ነበረብኝ፤ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት መታተም ከጀመረም በኋላ ማተሙ እንዲቆም ከበላይ ታዘዘ፤ እንደገና ሌላ ሚኒስትር ዘንድ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከተማ ይፍሩ ዘንድ ሄጄ ተነጋግረን ተፈቀደና ማተሙ ቀጠለና ታትሞ ወጣ።
አሁን ሳስበው ስለ ሶማልያ ድንበር ጉዳይ በማጥናቴና ጥናቱም ለአገሪቱም ለሚቀጥለውም ትውልድ ያገለግላል፤ ግንዛቤንም ያዳብራል ብዬ የሠራሁት ሥራ ባያስመሰግነኝም ያንን ያህል ተከታታይ እንቅፋቶች ይደቀኑብኛል ብዬ አልገመትሁም ነበር፤ በዚያን ጊዜ ዕድሜዬ ወደ ሠላሳ ሦስት ግድም ነበርና በሽማግሌዎቹ ዘመን ገና ልጅ ነበርሁ! በዚህ ዋና የአገር ጉዳይ ላይ ለመጻፍ የደፈርሁትም ልጅ በመሆኔ ሳይሆን አይቀርም፤ ሽማግሌው ብላታ መርስዔ ኀዘንማ ይኸው ሰማንያ ዓመታት ሙሉ ጭጭ ብለው ዛሬ በልጃቸው በኩል የሰማንያ ዓመት ታሪክ ይነግሩናል።
መጀመሪያ የብላታን ጽሑፍ ሳነብበው ንዴትና ሐዘን የተደባለቀበት ስሜት ይዞኝ ነበር፤ ምነው ቀደም ብለው በጊዜው ቢያወጡትና ብንጠቀምበት፣ ለምን ቆየ? ቀስ እያልሁ በራሴ ላይ የደረሰውን ሳስታውስ ንዴቴን ቀነሰልኝ እንጂ ሐዘኔን አላስቀረውም፤ ስለዚህ ለእኔ መርስዔ ሐዘን አልሆኑልኝም።
የዛሬ ሃምሳ ዓመት ግድም እኔ ይህንን የወሰን ጉዳይ ለማጥናት ስዳክር ዋናውን የወሰን ክልል መሪ በጅሮንድ ተሰማ ባንቴን ባላውቃቸውም ዋና ጸሐፊውን አቶ መርስዔ ኀዘንንና (በኋላ ብላታ) አቶ ዘውዴ በላይነህን (በኋላ ብላታ) ዐውቃቸው ነበር፤ እነዚህ ሰዎች በጣም ሊረዱኝ ይችሉ ነበር፤ ብዙ ድካምም ይቀንሱልኝ ነበር፤ አንድ አደጋና ድካም የነበረበት ልፋት ብቻ ላንሣ፤ በኢትዮጵያና በብሪታንያ ሶማሊላንድ (ብላታ መርስዔ ኀዘን እንደሚሉት በእንግሊዝ ጥገኛ የሱማሌ አገር) መካከል የተከለለው ወሰን ለወሰን ክለላ በአርአያነት የሚጠቀስ መሆኑን ዐውቅ ነበር፤ ለሌላ ጥናት ወደ ኦጋዴን ከተላከ ቡድን ጋር ሄጄ ስለነበረ ዕድሉን በመጠቀም ከቱግ ውጫሌ ጀምሮ እስከ ሦስቱ አገሮች (ኢትዮጵያ፣ የብሪታንያ ሶማሊላንድና የኢጣልያ ሶማልያ) መገናኛ ድረስ (48º ሰሜን/ 8º ምሥራቅ) ወሰኑን በሙሉ ለማለት ይቻላል ሄጄበታለሁ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ወሰኑን ተከትሎ ተሠርቶ የነበረው መንገድ ከጥቅም ውጭ ስለነበረ የመጣ ይምጣ ብዬ በሶማልያ ክልል ውስጥ በነበረው መንገድ እስከ መጨረሻው ሄድንበት፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ድንበሩን ተከትሎ የተሠራው መንገድ ቢበላሽም ወሰኑ በጣም ግልጽ ሆኖ ይታይ ነበር፤ ሆኖም በጥሩ የመካለል ሥራ በዓለም የሚጠቀስ ነው።
አንድ የሚያስደንቅና መነገርም ያለበት ነገር አለ፤ በብሪታንያ ሶማሊላንድና በኢትዮጵያ መካከል የተደረገውን ዓይነት መካለል በደቡብ ከኢጣልያ ሶማልያ ጋርና ከኬንያ ጋር፣ በምዕራብ ከሱዳን ጋር አልተደረገም፤ ከፈረንሳይ ሶማሊላንድ ሲባል ከነበረው ከጅቡቲ ጋር ደኅና የሚባል መካለል የተደረገ ይመስለኛል።
በአጼ ምኒልክ ዘመን በኢትዮጵያና በሱዳን ወሰን የክለላ ሙከራ ተደርጎ ነበር፤ ነገር ግን በኢትዮጵያ በኩል ሰው ስላልነበረ አንድ እንግሊዝ ብቻውን (ሻለቃ ግዊን)፣ በወሰኑ ክፍል ከነበሩት አገረ–ገዢዎች ትንሽ እየታገዘ በ1892 ዓ.ም. የሠራው ነው፤ እንግዲህ ከዚህ የክለላ ሥራ በፊትም ሆነ በኋላ በጥራቱና በዘላቂነቱ የሚወዳደር ሥራ አልተሠራም፤ ምን ያመለክተን ይሆን?
– ፬ –
በመጨረሻ የብላታ መርስዔ ኀዘን ልጅ አምኃ ይህንን ቢያንስ ሃምሳ ዓመት የዘገየ ታሪክ ለሕዝብ እንዲቀርብ በማድረጉ ከፍተኛ ምስጋና ይገባዋል፤ ምናልባትም ለሌሎችም አርአያ ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
መስፍን ወልደ ማርያም
ሚያዝያ 7/2003