ቀዳሚቃል

 

የኢትዮጵያ ሊቃውንት አራቱን ብሔራዊ የትምህርት ዓይነቶች በዕውቀት ያጠቃለለውን መምህር “አራት ዓይና” ይሉታል። የትምህርታችን ሥርዓት እንደሚያስረዳው የአንድ መምህር ግዴታ ከመምህሩ የወረሰውን ዕውቀት ለደቀ መዝሙሩ እንዳለ (ሳይቀንስ ሳይጨምር) ማውረስ ነው። የብሔራዊ ዕውቀታችንን መጠን ከአራቱ ዓይነት ዕውቀቶች አልፎ በየዘመኑ እያደገ እንዲሄድ ያደረገው አንዳንድ እንደክቡር ብላታ መርስዔ ሐዘን ወልደ ቂርቆስ ያሉ የወረሱት የማያጠግባቸው አምስት ዓይና ሊባሉ የሚገባቸው ተመራማሪ ምሁራን ጥረት ነው። እነዚህ “አምስት ዓይና’’ ሊቃውንት አእምሯቸው ሁል ጊዜ ስለሚራብ ዕውቀት ፍለጋ በሁሉ ቦታ ይገኛሉ። የውጭ ሀገር ፈላስፎች፥ የውጭ ሀገር ታሪክ ጸሐፊዎች፥ የውጭ ሀገር ድርሰቶች ወደሀገራችን ቋንቋ የተመለሱት በእነዚህ ተመራማሪዎች የዕውቀት ጥማት ነው።በእኛ ዘመን የኢትዮጵያን ዕውቀት በማዳበር ረገድ የአንደኛነቱን ቦታ የያዙት አምስት ዓይናው ብላታ መርስዔ ሐዘን ወልደ ቂርቆስ ናቸው። የትምህርት ጓደኞቻቸው ታላቅ ደብር የሚያስሾም ትምህርት ሲመርጡ ክቡር ብላታ መርስዔ ሐዘን የመረጡት የሚማረውና የሚያስተምረው አጥቶ ሊጠፋ የነበረውን ትምህርት ነበር። ለአማርኛ ቋንቋ ሰዋስው በማውጣት ፈር የቀደዱት ክቡር ብላታ መርስዔ ሐዘን ናቸው።

ክቡርነታቸው የትም ቦታ ለምንም ጉዳይ ቢሄዱ ዕውቀት ሳይዘርፉ አይመለሱም። በኢትዮጵያና በግብጽ ቅብጦች መካከል ተፈጥሮ ለነበረው ችግር መፍትሔ ፍለጋ ብዙዎች እንደ ክቡር ብላታ መርስዔ ሐዘን ወደግብጽ ሄደው ነበር፤ ዝርዝሩን ከሥር መሠረቱ የምናውቀው ግን ክቡርነታቸው ከጻፈልን መረጃ ነው። አንኮበር ደርሰው ሲመለሱ ባዶ እጃቸውን አልመጡም። የወይዘሮ ዘውዲቱ የንግሥ በዓል ላይ የተገኘ ሁሉ በሚጠፋው ግብዣ ላይ ሲያተኩር ክቡርነታቸው የሚወረስ ዕውቀት ይሰበስብ ነበር።

ጅጅጋ የራስ መኰንን ትምህርት ቤት ሥራ አስኪያጅነት ቢሾሙ መጽሐፈ ዜና ዓመት ዘ፲፱፻፳፭ ዓ. ም. የሚባል ብዙ ታሪክ የያዘ ዘገባ ሰጡን። ልጆች በርቱ እንማር፤ ባገር ፍቅር እንጠንክር፤ ብርሃን ሳለ ባንራመድ፥ አይረባንም የሌት መንገድ፤ እያሉ ልጆቹን ሀገር ፍቅር ያስተምሩ ነበር። ፊታውራሪ በየነ መርድና ወይዘሮ ሮማነ ወርቅ ተፈሪ በተክሊል ሲጋቡ ከቦታው ቢገኙ ዝርዝሩን በመመዝገብ የተክሊል ሥርዓት ምን አንደሚመስል አስተማሩን። ወልወል ላይ ከፋሺስቶች ጋር ስለተነሣው ግጭት ከኢትዮጵያ በኩል ምን ይባል እንደነበረ የምናውቀው ገና የክቡር ብላታ መርስዔ ሐዘን ወልደ ቂርቆስ ዘገባ ሲታተም ነው። የደጃዝማች ተሾመ ሸንቁጥን የአርበኝነት ታሪክ ምክንያት በማድረግ፥ በሙሉ ሸዋ በመንዝና በመርሐቤቴ አውራጃ የተደረገውን የአርበኞች ጦርነትና ውጤቱን መዝግበውልናል። እነዚህን ድርሰቶች ያነሣሣኋቸው የክቡርነታቸውን ማንነት ለማሳየት እንጂ ድርሰቶቻቸውን ዘርዝሮ ለመጨርስ አይደለም።

የባሕረ ሐሳብ ስሌት የተከበረ ዕውቀት ነው። ስሌቱን የሚያውቁት ጥቂቶች ሲሆኑ አንዱ ክቡር ብላታ መርስዔ ሐዘን ወልደ ቂርቆስ መሆናቸው አያስገርምም። እሳቸውን ከሌሎቹ የባሕረ ሐሳብ ስሌት ዐዋቂዎች የሚለያቸው ያው ዕውቀት የማዳበር ፍላጎታቸው እዚህም ላይ መታየቱ ነው። ይኸም በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በሁለት መልክ ይታያል፤ አንደኛ፥ ሲወርድ ሲዋረድ ከእኛ ዘመን የደረሰውን የባሕረ ሐሳብ ስሌት በአጭሩ ከአስተማሩን በኋላ፥ ለሰባ ዓመታት የሚያገለግሉ ዓመተ ምሕረትን ከዓመተ እግዚእ (AD) እና ከዓመተ ተንባላት (ዓመተ ሂጅራ፥ ዓመተ አጋር) ጋር የሚያገናዝቡ ሰንጠረዦች አዘጋጅተውልናል። ሁለተኛ፥ በሀገራችን ያልነበረውን የዓመተ ተንባላትን አወጣጥ ስሌት አምጥተውልናል። የኢትዮጵያ ሙስሊሞች በዓመተ ተንባላት ስለሚጠቀሙ፥ በዚህ አስተዋፃኦዋቸው የነበረውን ብሐራዊ ችግር አቃልለዋል። ይህ ክቡርነታቸው ያቃለለው ችግር የቱን ያህል እንደሆነ፥ በ፲፱፻፷፩ ዓ. ም. ከየመንግሥት ሠራተኞች ማስተዳደሪያ ጠቅላይ መሥሪያ ቤት የተጻፈላቸው ጥያቄና ክቡርነታቸው የሰጡት መልስ ያስረዳሉ። የደብዳቤዎቹ ፎቶግራፍ በአባሪ መልክ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ይገኛሉ። አገሪቷን ያለ አንድ ተጠያቂ ሊቅ የማይረሳት አምላክ ክብርና ምስጋና ይድረሰው።

የሀገሪቱ ትምህርት የዓመተ ተንባላትን ስሌት መጨመር እንዳለበት ግልጽ ነበር፤ ምክንያቱም ሊቃውንቱ የአንድን ድርጊት ዘመን ሲጽፉ ዘመኑን አንዳንድ ጊዜ በዓመተ ተንባላት ጭምር ይመዘግቡታል። ስሌቱን ግን ማንም ሊቅ ከሌሎቹ የባሕረ ሐሳብ ስሌቶች ጋር አላስተማረንም። ክቡር ብላታ መርስዔ ሐዘን የዕውቀቱን አስፈላጊነት በመገንዘባቸው ስናደንቃቸው፥ ዕውቀቱን በተለመደው የዕውቀት ጥማታቸው ከሚገኝበት ፈልገው አምጥተውታል። ከየትና እንዴት እንዳግኙት እንዲህ ሲሉ ይነግሩናል፤

ሊቃውንት አንዱን የዘመን ቊጥር ከሌላው ጋር በማነጻጸር ወይም በማገናዘብ የሚጽፉት፤ ጉዳዩን በሁለትና በሦስት ምስክር ለማረጋገጥ መሆኑ የታወቀ ነው። እኔም ለምስክርነት የቀረቡትን ጥቅሶች ለመረዳት ስለፈለግሁ ስለ ዓመተ ተንባላት ሥርዓተ ብተት ግብጻውያን ወዳጆቼን በመጠየቅና መጻሕፍትን በመመልከት ጥናት ጀመርኩ።

ጥናቶች ለኅትመት ካልበቁ የጋን ውስጥ መብራቶች ናቸው። ብዙዎቹ የክቡር ብላታ መርስዔ ሐዘን ድርሰቶች ከተከተቱበት ሳይወጡና ተማሪዎች ዕውቀታቸውን ሳያዳብሩባቸው ብዙ ዓመታት አልፈዋል። አሁንም ልጃቸው አቶ አምኃ መርስዔ ሐዘን የአባቱን ብሔራዊ አስተዋፅኦ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለማቅረብ በብሔራዊ ቁጭት ባይነሣ ኖሮ ድርሰቶቹ ከተከተቱበት ሳይወጡ ሌሎች ብዙ ዓመታት ሊያሳልፉ ምናልባትም ሊጠፉ ይችሉ ነበር። አቶ አምኃ ድርሰቶቹን ለኅትመት በሚያዘጋጅበት ጊዜ እንነጋገርና እንጻጻፍ ስለነበረ፥ እኔም መጽሐፍ ለማሳተም ሲሞከር የሚገጥሙትን ችግሮች በግሌ ስለማውቅ፥ ከዚህ ለማድረስ ብዙ እንቅፋት አንዳጋጠመውና ሁሉንም በትዕግሥትና በጭካኔ እንዳለፋቸው ልመሰክር እችላለሁ። አቶ አምኃ ለመታከትና ለችግር ሳይሸነፍ የክቡርነታቸውን መጻሕፍት በእጃችን እንዲገቡ ስላደረገ ከልብ የመነጨ ምስጋና ይገባዋል።

ጌታቸው ኃይሌ