አጭርየሕይወትታሪክ

የታሪክ ማስታወሻ

የዚህ ታሪክ ጸሐፊ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ (ብላታ) መጋቢት 17 ቀን 1891 ዓ.ም. ሸዋ ጅሩ ውስጥ እምቧጮ መግደላዊት በተባለ ስፍራ ተወለዱ፡፡ አባታቸው አለቃ ወልደ ቂርቆስ አልታመን ይባላሉ፡፡ እሳቸውም በደብረ ሊባኖስና በእንጦጦ ማርያም የቤተ ልሔምን መዝገበ ድጓ ሲያስተምሩ የነበሩና በዜማ መምህርነት የታወቁ ናቸው፡፡ እናታቸው ወይዘሮ የሸዋ ወርቅ ምናጣ ይባላሉ፡፡ የአባታቸው አጎት አለቃ ገብረ ክርስቶስ የብሉይና የሐዲስ ሊቅና የቅኔ መምህር የነበሩ በንጉሥ ኃይለ መለኮት፣ በአጼ ዮሐንስና በአጼ ምኒልክ ቤተ መንግሥት እጅግ የተከበሩ ሰው ነበሩ፡፡
መርስዔ ኀዘን በ1896 ዓ.ም. ወደ እንጦጦ መጥተው ከአባታቸው ዘንድ ንባብ ተማሩና በሰባት ዓመታቸው ዳዊት ደገሙ፡፡ ቀጥሎም የዜማ ትምህርት ጀምረው ጾመ ድጓና ድጓ ተማሩና ቅኔ ተቀኙ፡፡ ከዚህ በኋላ የመጻሕፍተ ሐዲሳትን ትርጓሜ ከራጉኤሉ ከመምህር ወልደ ጊዮርጊስ ተማሩ፡፡
በ1912 ዓ.ም. ስለ ጽሕፈት ሥራ በደመወዝ ተቀጥረው በስመ ጥሩው ሊቅ በአለቃ ገብረ መድኅን ሥር የመንግሥት ሥራ ጀመሩ፡፡ ሥራውም የአረጋዊ መንፈሳዊን ትርጓሜ ልዩ ሙያ ካላቸው ሊቅ ከመምህር ደስታ (የመምህር አካለ ወልድ ደቀ መዝሙር) ተምሮ የትርጓሜውን ረቂቅ ማውጣትና፣ በባለሙያው ሊቅ አረጋግጦ ንባቡን ከነትርጒሙ ለኅትመት ማዘጋጀት ነበር፡፡ ይህ አረጋዊ መንፈሳዊ ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኰንን በ1920 ዓ.ም. ድሬዳዋ ላይ ያሳተሙት ነው፡፡
ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኰንን ብርሃንና ሰላም ብለው የሰየሙት አንድ አዲስ ጋዜጣ ታኅሣሥ 23 ቀን 1917 ዓ.ም. በማተሚያ ቤቱ ዲሬክተር በአቶ ገብረ ክርስቶስ ተክለ ሃይማኖት መሪነት ሲመሠረት መርስዔ ኀዘን ወደ ጋዜጠኛነት ተዛውረው በዋና ጸሐፊነት ይሠሩ ጀመር፡፡ ከአራት ወር በኋላም ሚያዝያ 19 ቀን 1917 ዓ.ም. የተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ተመርቆ ሲከፈት የግዕዝና የአማርኛ አስተማሪ ሆነው ወደ ትምህርት ቤቱ ተዛወሩ፡፡ በዚህ ጊዜ ያሰናዱት ትምህርተ ሕፃናት የተባለች መጽሐፍ በልዑል አልጋ ወራሽ ፈቃድ ግንቦት 1 ቀን 1917 ዓ.ም. ታትማ ወጣችና የግብረ ገብ ትምህርት ማስተማሪያ ሆነች፡፡ መርስዔ ኀዘን በዚሁ ጊዜ እንግሊዝኛ ለመማር በትጋት ይጣጣሩ ጀመር፡፡
ከአንድ ዓመት በኋላ ጽፈው ያቀረቡዋት በአዲስ ሥርዓት የተሰናዳ የአማርኛ ሰዋስው በማጥኛ ደብተር እየተገለበጠ ወዲያው የተማሪዎች መማሪያ ሆኖ በአገልግሎት ላይ ዋለ፡፡ ይህ ሰዋስው ከጠላት ወረራ በኋላ በ1935 ዓ.ም. ታትሞ የወጣው ነው፡፡ ለግማሽ ምዕት ዓመታት ያህል ለኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች መደበኛ ማስተማሪያ ሆኖ አገልግሏል፡፡
አቶ መርስዔ ኀዘን በ1922 ዓ.ም. ወደ ጅጅጋ ከተማ ተዛውረው ከዚያ ለቆመው ለልዑል ራስ መኰንን ትምህርት ቤት ዋና ሹም በመሆን አምስት ዓመት አገልግለዋል፡፡ በዚሁም ጊዜ በተጨማሪ ከተሰጣቸው ሥራዎች ውስጥ በወሰን ክልል ሥራ ላይ ከወሰን ተከላካዮች ጋር የተፈጸመ አገልግሎት ይገኝበታል፡፡ በ1924 ዓ.ም. በታኅሣሥ ወር የተጀመረው የኢትዮጵያና የእንግሊዝ ሱማሌላንድ የወሰን ክልል ኮሚሽን ሥራውን እስካበቃበት እስከ 1927 ዓ.ም. የካቲት ድረስ በዋና ጸሐፊነት ሦስት ዓመት ከሁለት ወር አገልግለዋል፡፡ የክልሉ ሥራ ከደርኬንጌኞ አንሥቶ እስከ ጃሌሎ ድረስ የተዘረጋው ርዝመቱ ከሰባት መቶ ኪሎ ሜትር በላይ በሆነው የወሰን መስመር ላይ ሲሆን ሐበር አወልንና ገደቡርሲን ኢሳን በመርገጥ የተሠራ ነበር፡፡
በመጨረሻም ኢጣልያኖች በውጋዴን ውስጥ ወልወል ላይ ዳር 26 ቀን 1927 ዓ.ም. ረቡዕ አደጋ በጣሉ ጊዜ አቶ መርስዔ ኀዘን በስፍራው ላይ ተገኝተው ከወሰን ተከላካዮቹ ጋር ሆነው አደጋውን ተከላክለዋል፡፡ በ1927 ዓ.ም. ሰኔ 10 ቀን የትልቁ ወህኒ ቤት ዲሬክተር ሆነው ተሾሙ፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ በተከተለውም በጠላት ወረራ ዘመን በጅሩና በአድአ በሌላም ስፍራ እየተዘዋወሩ ሕይወታቸውን አትርፈዋል፡፡

ከጠላት ወረራ በኋላ የመንግሥት ሥራ አገልግሎት

የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ 1933 – 36 ዓ.ም.
የጋዜጣና ማስታወቂያ ጽሕፈት ቤት ዋና ዲሬክተር
1936 ዓ.ም.
የታሪክና የቤተ መንግሥት ዜና ማሰናጃ ጽሕፈት ቤት ዲሬክተር 1936 – 46 ዓ.ም.
የብላታ ማዕርግ ሚያዝያ 1936 ዓ.ም.
የፍርድ ሚኒስቴር ም/ሚኒስትር 1941 – 50 ዓ.ም.
የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ዓቃቤ ጉባዔ 1950 – 54 ዓ.ም.
የሕግ መወሰኛ ም/ቤት አባልና የሕግ ኮሚቴ ሊቀ መንበር 1950 – 63 ዓ.ም.
የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ም/ፕሬዜዳንት 1954፣ 56፣ 60 – 61 ዓ.ም.
የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ተጠባባቂ ፕሬዜዳንት 1960 ዓ.ም.
የታሪካዊ ቅርሶች አስተዳደር አማካሪ 1963 – 66 ዓ.ም.
ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ በመደበኛ ሥራቸው ላይ ደርበው የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሹም ሆነው ለ14 ዓመታት፤ የሕዝብ ጤና ሚኒስቴር ተጠባባቂ ሹም ሆነው ለአንድ ዓመት ሠርተዋል።
እንዲሁም በአያሌ ቦርዶች በአባልነትና በሊቀ መንበርነት አገልግለዋል። ከነኚህም ዋኖቹ የሚከተሉት ናቸው። የዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ቦርድ ሊቀ መንበር፣ 1946-54 ዓ.ም. ፤ የትምህርትና የሥነ ጥበብ ሚኒስቴር ቦርድ አባል፣ 1940 – 54 ዓ.ም. ፤ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ቦርድ አባልና ምክትል ሊቀ መንበር፣ 1942 – 66 ዓ.ም. ፤ የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር
(ወ. ወ. ክ. ማ) ቦርድ አባልና ምክትል ፕሬዜዳንት 1941 – 1966 ዓ.ም.።

በልዩ ትእዛዝ የፈጸሟቸው አገልግሎቶች

ብላታ መርስዔ ኀዘን ከመደበኛ ሥራቸው ደርበው አያሌ ልዩ ልዩ ሥራዎችን እየታዘዙ ሠርተዋል። ከነኚህም ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው።
የኢትዮጵያና የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ድርድር
ኅዳር 1 ቀን 1940 ዓ.ም. ብላታ መርስዔ ኀዘን ኢትዮጵያ የራሷን ፓትረያርክ እንድትሾም በኢትዮጵያና በእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያናት መካከል በሚደረገው ድርድር ተካፋይ እንዲሆኑ ተመረጡ። ብላታ መርስዔ ኀዘን እስከ ድርድሩ ፍጻሜና የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትረያርክ፣ የአቡነ ባስልዮስ ሢመት እስኪፈጸም ድረስ ተሳታፊ ሆነው አገልግለዋል። ዝርዝር ታሪኩንም «ሢመተ ሊቀ ጳጳሳት ኢትዮጵያዊ» እና «የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትረያርክ» በሚል ርእስ ባዘጋጇቸው መጻሕፍት ጽፈውታል።
የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ማረም ኮሚቴ
የካቲት 27 ቀን 1939 ዓ.ም. የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ማረም ኮሚቴ ሊቀ መንበር ሆኑ። ለዚህ ሥራ ተመርጠውና ታዝዘው በልዩ ልዩ ጊዜ የሥራ ተባባሪ የሆኑት ሊቃውንት ብዙ ነበሩ። ነገር ግን እስከ ሥራው መጨረሻ ድረስ ምንም ሳይለዩ ሥራውን በመቀጠል ላይ የነበሩት፤ በብሉይ ኪዳን ክፍል ሚስተር ግራሃምና ብላታ መርስዔ ኀዘን፤ በሐዲስ ኪዳን ክፍል ቄስ ማቲውና አለቃ አርአያ ሥላሴ ወሮታ ነበሩ። የተሻሻለው የአማርኛ ሐዲስ ኪዳን በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት በ1947 ዓ.ም. ፤ ጠቅላላው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ብሉይ ኪዳንና ሐዲስ ኪዳን) ሐምሌ 16 ቀን 1952 ዓ.ም. በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ታትሞ ወጥቷል።
የፍትሐ ነገሥት ኮሚሲዮን
መጋቢት 17 ቀን 1946 ዓ.ም. በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትእዛዝ የፍትሐ ነገሥት ኮሚሲዮን (የኮዲፊኬሽን ኮሚሲዮን) ሲቋቋም የኮሚሲዮኑ ሊቀ መንበር የፍርድ ምክትል ሚኒስትሩ ብላታ መርስዔ ኀዘን ነበሩ። የኮሚሲዮኑ አባላት ሦስት የታወቁ የአውሮጳ የሕግ ፕሮፌሰሮችና የበሰለ የባህልና የሕግ ዕውቀት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ነበሩ።
የኮሚሲዮኑ ዓላማ በፍትሐ ነገሥትና በኢትዮጵያ የነበሩትን ልማዶችና ባህሎችን መሠረት በማድረግ የወንጀል፣ የፍትሐ ብሔር፣ የንግድና የባሕር ሕጎችን ማዘጋጀት ነበር። የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በ1949 ዓ.ም. ፣ የፍትሐ ብሔር ሕግ በ1952 ዓ.ም. የንግድና የባሕር ሕጎች በ1953 ዓ.ም. በፓርላማ ጸድቀው ንጉሠ ነገሥቱም አጽድቀዋቸው ሕግ ሆነው ወጥተዋል። እነኚህ ሕጎች እስካሁን በመሠረቱ አልተቀየሩም፤ ከአንዳንድ ማሻሻያዎች በስተቀር አሁንም ድረስ በኢትዮጵያም በኤርትራም እየተሠራባቸው ናቸው።
መጽሐፈ ቅዳሴ
በ1918 ዓ.ም. 14ቱ መጽሐፈ ቅዳሴ ታትሞ ወጥቶ ነበር። በ1942 ዓ.ም. የወጣውን መጽሐፈ ቅዳሴ ያዘጋጁት ብላታ መርስዔ ኀዘን ናቸው። በ1942 ዓ.ም. ተሻሽሎ የታተመው መጽሐፈ ቅዳሴ ውስጥ ሊጦን፣ መስተብቊዕና ዘይነግሥ ተጨምረውበታል።
የፍትሐ ነገሥት ንባብና ትርጓሜ ሥራ
በ1960 ዓ.ም. የፍትሐ ነገሥት ንባብና ትርጓሜ የሚሠራ ኮሚቴ ተቋቋመ። የኮሚቴው ሰብሳቢ ብላታ መርስዔ ኀዘን ሲሆኑ፤ አባላቱ ሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም ወርቅነህ (በኋላ አቡነ መልከ ጼዴቅ)፣ ብላታ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ፣ መልአከ ሰላም ሳሙኤልና መልአከ ብርሃን አድማሱ ነበሩ። ሥራው አንድ ዓመት ተኲል ወስዶ በ1962 ዓ.ም. ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ታትሞ ወጥቷል።

የአማርኛ መርሐ ልሳን
ሰኔ 20 ቀን 1964 ዓ.ም. የአማርኛ መርሐ ልሳን (አካዳሚ) ሲቋቋም ብላታ መርስዔ ኀዘን አባል ሆነው ተመረጡ። የመርሐ ልሳኑ ዓላማ የመንግሥቱን ቋንቋ አማርኛን ማዳበርና የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ እንዲስፋፋ ማበረታታት ነበር። ጡረታ እስከወጡበት ዘመን ድረስ በመርሐ ልሳኑ አባልነት አገልግለዋል።
በ1964 ዓ.ም. ብላታ መርስዔ ኀዘን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ሽልማት ተሸላሚ ሆኑ።
ብላታ መርስዔ ኀዘን በ1966 ዓ.ም. ጡረታ ወጡ። ከጠላት ወረራ በፊት 16 ዓመት ከ4 ወር ከጠላት ወረራ በኋላ 32 ዓመት ከ10 ወር በድምሩ 49 ዓመት ከ2 ወር በቅንነትና በታማኝነት ሀገራቸውንና መንግሥታቸውን አገልግለዋል።
ጥቅምት 19 ቀን 1971 ዓ.ም. ብላታ መርስዔ ኀዘን የቀኑን ሥራቸውን ጨርሰው ወደ መኝታቸው ሄዱ። ከዚያም በተኙበት በ79 ዓመታቸው ካለ ምንም ጻዕር ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተው ሥርዓተ ቀብራቸው ጥቅምት 21 ቀን 1971 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አቦ መካነ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ተፈጸመ።

በብላታ መርስዔ ኀዘን የተደረሱና የተዘጋጁ

ትምህርተ ሕፃናት፣ 1917 ዓ.ም.
የአማርኛ ሰዋስው በአዲስ ሥርዓት የተሰናዳ፣ 1935 ዓ.ም.
የአማርኛ ሰዋስው 1-2ኛ ክፍል፣ 1936 ዓ.ም.
የአማርኛ ሰዋስው መክፈቻ፣ 1936 ዓ.ም.
የትእምርተ መንግሥት ታሪክ፣ 1936 ዓ.ም.
የቤተ ክርስቲያን ዜና መጀመሪያ ቊጥር፣ 1938 ዓ.ም.
ግ ን ነ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጐንደርን የመጐብኘታቸው ታሪክ፣ 1939 ዓ.ም.
ዐውደ መዋዕል፤ 1939 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ መዝገበ ዕለታት፣ 1939 ዓ.ም.
የንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ዕረፍት መታሰቢያ፣ 1940 ዓ.ም.
ሢመተ ሊቀ ጳጳሳት ኢትዮጵያዊ፣ 1942 ዓ.ም.
የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትረያርክ፣ 1956 ዓ.ም.
የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ፣ 1999 ዓ.ም.
የዘመን ታሪክ ትዝታዬ ስለ ራሴ የማስታውሰው፣ ዋሺንግተን ዲሲ፣ 2001 ዓ.ም.
የዘመን ታሪክ ትዝታዬ ስለ ራሴ የማስታውሰው፣ አስቴር ነጋ አሳታሚ ድርጅት፣ አዲስ አበባ፣ 2002 ዓ.ም.
ትርጒም ሥራ አዘጋጅተው ያሳተሟቸው መጻሕፍት
ጥበብን መፈለግ 1-3ኛ መጽሐፍ፣ 1946 ዓ.ም.
ሔሮዶቱስ የጥንት ታሪክ 1-4ኛ መጽሐፍ፣ 1948 ዓ.ም.
ጽሑፎችን ሰብስበው ያዘጋጇቸውና የታተሙ መጻሕፍት
ፍሬ ከናፍር ዘቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ 1-6ኛ መጽሐፍ፣ 1944 ዓ.ም.
ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የተዘጋጁ የቅዱሳት መጻሕፍት ሥራዎች።
መቅድመ ወንጌል ንባብና ትርጓሜው፣ 1920 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዜና፣ 1938 ዓ.ም.
ከሊቃውንት ጋር የተሠሩ
አረጋዊ መንፈሳዊ ንባብና ትርጓሜ፣ 1920 ዓ.ም.
መጽሐፈ ሲራክ፣ 1914 ዓ.ም.
ሰባዓቱ ኪዳናት፣ 1920 ዓ.ም.
የቤተ ክርስቲያን ጸሎት በግዕዝና በአማርኛ፣ 1942 ዓ.ም.
መጽሐፈ ቅዳሴ በግዕዝና በአማርኛ፣ 1920 ዓ.ም.
The Liturgy of the Ethiopian Church 1959
(Translated by Rev. Marcos Daoud, Revised by H.E. Blatta Marse Hazen)
በኮሚቴ የተሠሩ
መጽሐፍ ቅዱስ በአማርኛ፣ በብላታ መርስዔ ኀዘን ሊቀ መንበርነት (1939 – 53 ዓ.ም.) ተሠርቶ የታተመ።
ፍትሐ ነገሥት በግዕዝና በአማርኛ፣ በብላታ መርስዔ ኀዘን ሊቀ መንበርነት (1962 – 63 ዓ.ም.)
ተሠርቶ የታተመ።
ያልታተሙ።
የኢትዮጵያና የእንግሊዝ ሱማሌላንድ የወሰን ክልል ታሪክ
የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት 1923 – 1927
የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት 1934 – 1939
በአንኮበር ከተማ የሸዋን ነገሥታት መቃብር መጐብኘት ሰኔ፣ 1937
አስማተ ሙታን፣ ለታሪክ ምርምር የሚረዳ የሙታን ማስታወሻ።
የዘመናት ማገናዘቢያ፤ ዓመተ ምሕረት፣ ዓመተ ዩልዮስ፣ ዓመተ ሰማዕታት፣ ዓመተ ተንባላት።