የታሪክ ማስታወሻ

 
መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ፤ አንድ ለእናቱ ለኢትዮጵያ
አንተ ቀጥቀጥትከ አርእሰቲሁ ለዕበድ፤
ወወሀብኮሙ ሰዋስዎሙ ለዘሕዝበ ኢትዮጵያ ውሉድ።
ክቡር ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ ለኢትዮጵያ የሰጡትን ልባዊ አገልግሎትና እሳቸውንም በአካል የሚያውቅ ሰው በየምእት ዓመት አንድ ጊዜ የሚታዩ የዕውቀትና የጥበብ ሰዎች ካሉ ክቡርነታቸው አንዱ መሆናቸውን አይጠራጠርም። ይኸንን ለማለት የደፈርኩበት ምክንያት ታሪካቸውን በቅርቡ ከሚታተመው “ትዝታዬ ስለራሴ የማስታውሰው። 1896-1922 ዓ.ም. ” ከሚለው ትዝታቸውና ከዚህም መጽሐፍ እየጠቀስኩ በአጭሩ ስመዘግብ ይታያል።
ክቡር ብላታ መርስዔ ኀዘን መጋቢት 17 ቀን 1891 ዓ.ም. (March 25 1899) ከደብረ ሊባኖሱ፣ በኋላም የእንጦጦ ማርያሙ የድጓ መምህር ከአለቃ ወልደ ቂርቆስ አልታመንና ከወይዘሮ የሸዋ ወርቅ ምናጣ እምቧጮ፣ ጅሩ፣ ላይ ተወለዱ። ዘመዶቻቸው፣ “በተወለደ በአራት ዓመት ከአራት ወር ከአራት ቀን ትምህርት የሚጀምር ልጅ ትምህርቱ ይገለጥለታል” በሚለው እምነት ተመርተው ቊጥሩ ሲሞላ በቅርባቸው ለሚገኝ አስተማሪ ሰጧቸው። እምነቱ መሠረተ ቢስ ቢሆንም ይዟል። ግን የአራት ዓመትን ልጅ ጨዋታ ከልክሎ ትኩረቱን ቀኑን ሙሉ በፊደል ላይ እንዲያውል ማስገደድ የቱን ያህል ጭንቅ እንደሆነ በዚያ ያለፈ ሁሉ ያውቀዋል። ልጆች አርጩሜውን ታግሠው እያለቀሱ ሲታዘዙ፣ ብላታ አጠገባቸው ካለው በደበጅ ገደል ገብተው ከትኩረቱም፣ ከፊደሉም፣ ከአርጩሜውም ለመገላገል ፈልገው ነበር። የአክስታቸው የእመዬት በሰሙ እና የኢትዮጵያ አምላክ ፍርሃትን በገላጋይነት ላከላቸው።
ብላታን ትምህርት ያስጠላቸው ትምህርቱ ሳይሆን ሥርዓቱ መሆኑን ዘመዶቻቸው ባይገነዘቡም ትምህርቱ እንዲቀርላቸው አደረጉላቸው፤ ተዉትና ውሏቸው ጨዋታ ሆነ። ብላታ ማን እንደሆኑ ቀደም ብዬ ስለማውቅ፣ ይኸንን ከትዝታቸው ሳነብ የክቡርነታቸው ክፍል ከካህን ያሬድ አክሱማዊና ከአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ጋር መሆኑ ገባኝ። ቅዱስ ያሬድ ትምህርቱን ጥሎ ሄዶ ነበር፤ በትል ድካምና ብርታት መልክቱ ደርሶት ለኢትዮጵያ ታላቅ አስተዋፅኦ አበረከተ፤ አባ ጊዮርጊስም ትምህርት አልገባ ስላላቸው ጨዋ ወታደር እንዲሆኑ ተፈርዶባቸው ነበር። እመቤታችን ተገልጣ ስላበረታታቻቸው ታላቅ የግዕዝ ዜማና የሥነ ጽሑፍ ሰው ሆኑ። ብላታም በአክስታቸውና በእንጀራ እናታቸው በወይዘሮ ወለተ እስራኤል አበረታታችነት ወደ ትምህርት ዓለም ተመልሰው፣ “ፊደል በብዙ ድካም ታለፈችና” እነሆ የመላ ኢትዮጵያ ተማሪዎች አስተማሪ ሆኑ። የትውልድን ቦታ መልአክ ይወስነው ይመስል ብላታ በሊቃውንት ዘመዶች ማህል ተወልደው የወደፊት ሕይወታቸው የሊቅነት ሆነ። አባታቸው አለቃ ወልደ ቂርቆስ በአንድ በኩል የካህን (የመምሬ አልታመን) ልጅ ሲሆኑ በሌላ በኩል ታላቁ የብሉይ፣ የሐዲስ፣ የቅኔ ሊቅ አለቃ ገብረ ክርስቶስ አጎታቸው (የናታቸው የወይዘሮ እስታሉ ወንድም) ነበሩ። “አለቃ ገብረ ክርስቶስ በንጉሥ ኃይለ መለኮትና በአጼ ምኒልክ ቤተ መንግሥት እጅግ የተከበሩ ሰው ነበሩ። አጼ ዮሐንስ በ1873 ዓ.ም. አራት ጳጳሳት ለማስመጣት ወደ ግብጽ አራት መልክተኞችን በላኩ ጊዜ ከሸዋ በኩል የተላኩት መልክተኛ አለቃ ገብረ ክርስቶስ ነበሩ።” በየመጽሐፈ ድጓው ስማቸው የተመዘገበው ሊቀ ካህናት መርሻ የአለቃ ወልደ ቂርቆስ የትምህርት ጓደኛ ነበሩ። አለቃ ወልደ ቂርቆስ በአስተማሪነት ታላላቅ ሊቃውንት አፍርተዋል።
ወደፊት እንደምናየው የብላታ ስመጥርነት ከሊቃውንቱ አንዱ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ስጦታቸውን “አንድ ለእናቱ ለኢትዮጵያ” በሚያሰኝ ደረጃ ለሀገር መቀደሳቸው ነው።
ብላታ ወደ ትምህርት የተመለሱት አሁን ከደብረ ሊባኖስ መጥተው የዲልዲላ (የእንጦጦ) ማርያም የድጓና የፊደል መምህር ከሆኑት አባታቸው ዘንድ ነበር። ሆኖም የተማሪ ጠሮዎች እነ ቁንጢጥ፣ እነ አርጩሜ (ተማሪዎች “በላዔ ሰብእ”- -”ሰው በላ- - የሚሏት የአባታቸው አለንጋ) አልቀሩላቸውም፤ እንዲያውም አባታቸው ቤት በመቀመጣቸው፣ “ሥርዓት” የሚሉትን የአገልጋይነት ሥራ በተጨማሪ በኩርኩም እንዲማሩት ተደረጉ። ፊደል እንዳወቁ ወደ ገበታ ሐዋርያ መሄድ ሥርዓት ነውና ወደዚያ ሄዱ። ገበታ ሐዋርያ የሚባለው ከመጀመሪያው የዮሐንስ መልእክት የመጀመሪያው ምዕራፍ ነው፤ መማሪያው ሐዋርያ ለመሆኑ ስሙም ያመለክታል። ብላታ የተማሩት “ገበተ ሐዋርያ (ግን) ከእንጦጦ ማርያም ዕቃ ቤት የመጣ ገድለ አባ ሊባኖስ ይባላል።”
ከፊደል ወደ ገድለ አባ ሊባኖስ የተሻገረ ተማሪ የሚቀጥለውን ትምህርት ለመፈጸም ብዙ ጊዜ የማይወስድበት ይመስል ዳዊታቸውን በአጭር ጊዜ ደገሙ። ወዲያው የዜማ ትምህርት ጀመሩ፤ የቃል ትምህርት የሚባሉትን (ውዳሴ ማርያምን፣ መስተጋብእን፣ አርባዕትን፣ አርያምን፣ ሠለስትን) እና ጾመ ድጓን ጨርሰው በተወለዱ በስምንት ዓመታቸው (“በ1899 ዓ.ም፣ መጀመሪያ ላይ”) ድጓ መማር ጀመሩ። ብላታ ካበረከቱን ትዝታቸው ውስጥ ከዚህ በታች ያለው ይገኝበታል፤
ጃንሆይ አጼ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ “የመስከረም ማርያምን በዓል ለማክበር እንጦጦ መጥተዋል። ማኅሌቱ ደምቆ ካህናቱ ሲያሸበሽቡ ጃንሆይ ከቅድስት ሆነው ይመለከቱ ነበር። በምልጣን ጊዜ እስመ ለዓለም መቃኘት የተለመደ ሥርዓት ነው። በዚህ ቀን የደብሩ አለቃ መልአከ ፀሐይ አፈወርቅ እኔና ጓደኛዬ ገብረ ኪዳን ወረደ እንድንቃኝ አዘዙን። በዚያ ጊዜ ሁለታችንም የዘጠኝ ዓመት ዕድሜ ነበርን። ... እንግዲህ እኛ ወደ ቅኔ ማኅሌት መካከል ገባን። ቁመታችን ገና ትንሽ በመሆኑ በነጋሪት ላይ አቆሙንና እስመ ለዓለሙን በዜማ ቃኘን። ...በዚህ ጊዜ ጃንሆይ ቀጭን ድምፃችንን በመስማትና በዕድሜያችን ማነስ ተደንቀው፣ ́እውነት እነዚህ ልጆች እስከዚህ ድረስ ተምረው ነው ወይ́̕ ብለው መልአከ ፀሐይ አፈወርቅን ጠየቁ።”
ብላታ ቅኔ መማር ሲጀምሩ የዓሥር ዓመት ሕፃን ነበሩ፤ በዓመቱ “ሰኔ 12 ቀን 1902 ዓ.ም. ዕለተ እሑድ ቅኔ አስቀኙኝ። በዚህ ጊዜ የተሰማኝ ደስታ ከመጠን ያለፈ ነበር” ይላሉ። እንዴት ከመጠን ያለፈ ሊሆን ይችላል? ቅኔ ከተቀኙ በኋላ ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ አባታቸው ስላዘዟቸው እዚያው ቅኔ እተቀኙበት እንጦጦ ቆዩ። ስለዚያ ጊዜ ትዝታቸው እንዲህ ይላሉ፤
የትምህርት ጓደኞቼ አንድ ሙሉ ቤት ብቻ ቅኔ እየቆጠሩ ሲነግሩ እኔ ግን በየቀኑ ሦስት ሙሉ ቤት ቅኔ እንድቈጥርና ለአስተማሪዬ እንድነግር አባቴ ልዩ ትእዛዝ ሰጡኝ። ለመቆጣጠር እንዲመቻቸውም ለአስተማሪዬ የነገርሁትን ሁሉ በየቀኑ ለእርሳቸው እንዳቀርብላቸው አዘዙኝ። ለጨዋታ የሚበቃ ጊዜ ባለመስጠታቸው ምንም እንኳ ብበሳጭ ትእዛዙን ተቀብዬ በመጀመሪያው 4 ወሮች ላይ ፈጸምሁ። በኋላ ግን ሰለቸኝና ትእዛዙን እያጓደልሁ ወደ ጨዋታ እሄድ ጀመር። በዚህ ምክንያት በባለ ቀለበት እግር ብረት አስረው እዚያው እተማሪ ቤቱ አስቀመጡኝ።
በዚህ ጊዜ ነፃ ለመውጣት ማንም ታዛቢ “አበጀህ” የሚላቸውን ፈጸሙ፤ በድጓና በቅኔ የተመረቀ የዓሥራ አንድ ዓመት ልጅ ለምን ጨዋታ አማረህ የሚሏቸውን አባት የእግር ብረት ሰብረው ጠፉ፤ አባታቸውን ሸሹ። ሸሽተው አዲስ ዓለም በነበሩበት ጊዜ ቢመቻቸውም አባታቸውን ከመፍራት ነፃ ሊሆኑ አልቻሉም። የአባታቸውን ወዳጆች በብዛት ስለተገናኙና ስላወቋቸው ምናልባት ያሉበትን ይነግሩባቸውና መጥተው ይይዟቸው መስሏቸው በስጋት ከዚያም መሸሽ ነበረባቸው። በሰላሌ በኩል ወደ ዘመዶቻቸው ለመሄድ “ብቻዬን ሆኜ በዚያ በማላውቀው አገርና መንገድ እኳትን ጀመር፤ ጊዜው እየመሸ ሄደ። (ከዛፍ ስር ተጠግቼ አደርኩ) ... ጨለማውና ብርዱ ከባድ ነበር። እስከ ዶሮ ጩኸት ድረስ እንቅልፍ ሊወስደኝ አልቻለም። ነፋስ የዛፉን ቅጠል ባንኮሻኮሸው ቊጥር ጅብ ሊበላኝ ወይም ጋኔን ሊያንቀኝ የመጣ እየመሰለኝ እፈራ ነበር” ይሉናል። የክቡር ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ ትዝታዬ ዋና የታሪክ ምንጭ ብቻ ሳይሆን የሚወደውን ልጅ የሚያሳድግ ሁሉ ሊያነበው የሚገባ ለዘብተኛ ግን ጽኑ ተግሣጽ ነው።
ብላታ ያንን ሁሉ ዕውቀት ከሰበሰቡና የበለጠ ወደፊት ለመግፋት ችሎታው እያላቸው፣ ትሕትናቸው ጥሪያቸውን ሸፍኖባቸው፣ የወምበር (የዳኛ) የግል ጸሐፊና አሽከር ሆኑ። በዚሁ ሥራቸው የወምበሩን የማኅተም ኮሮጆና የወምበሩን ጠጅ መጠጫ ባለ ማኅደር አንድ አፈ ድስት ብርሌ በአንገታቸው ላይ አንጠልጥለው ጌታቸውን ሲከተሉ፣ መልአኩ በከንቲባ ሕለተ ወርቅ ተመስሎ ያገኛቸውና፣ የጥሪያቸውን መንገድ እንዲህ ሲል ይጠርግላቸዋል፤ “ኸረ በል ድጓና ቅኔ የተማርከው እንዲህ ለመሆን ኖሮአል? አህያ ይመስል የጓዝ መጫኛ ትሆናለህ፣ ... አሁንም ይህን ሥራ እርግፍ አድርገህ ትተህ ወደ ትምህርትህ በቶሎ እንድትመለስ እመክርሃለሁ።”
ምክሩን ተቀብለው ሥራውን ለመተው ዕድል ሲያጋጥማቸው ወደ ትምህርት ዓለም ተመለሱ። ዕድሜያቸው ዓሥራ ሰባት ዓመት ሲሆን ትርጓሜ ሐዲሳት መጻሕፍትን ቀጥሎም ሊቃውንቱን (አፈወርቅንና ቄርሎስን) ከዘመኑ ሊቃውንት ጠንቅቀው አጠኑ። የአፈወርቅ ድርሳን መጽሐፍ ቢቸግራቸው በቅርብ ሊደርሱበት የሚችሉት መጽሐፍ አለ፤ ቀን ሲያዝባቸው ሌሊት እየተዋሱ በዓሥራ ሰባት ሌሊት ቀድተው ባለመጽሐፍ ሆኑ።
ብላታ ቅዱሳት መጻሕፍትና ባህል የሚያዙትን ትሕትና በተጠናቅቆ የሚጠብቁና ሰው የማይነኩ ሰላማዊ ደግ ሰው መሆናቸውን ለማወቅ ብዙ ጊዜ አይወስድም። ስለትምህርት ጓደኞቻቸው እንጂ ስለራሳቸው ጉብዝና መናገር ፈጽሞ አይሆንላቸውም። ትዝታቸውን ሳነብ የላቀ ችሎታ ያላቸው መሆኑን ያወቅሁት የየደረጃውን ትምህርት ከደረጃው አስቀድመው ሲጨርሱት በማየቴ ብቻ ሳይሆን በአንድ ሊያስወግዱት ባልቻሉት ዘገባቸው ጭምር ነው። እንዲህ ይላሉ፤
በዚህ ወራት (የሐዲስ ትርጓሜ) ትምህርቴ ከሐዋርያ መልእክት ደርሶ ነበርና ከቀድሞው ይልቅ ትምህርቱን ስለ ተላመድሁት በማጥናት ረገድ ምንም እንኳ ከዕውር ወልደ ጊዮርጊስ ደረጃ ባልደርስ ወደዚያው ለመጠጋት እሞክር ጀመር። አንድ ቀን የዮሐንስን መልእክት በመማር ላይ ሳለሁ አስተማሪዬ ጉባኤውን አንድ ጊዜ ተረጐሙልኝና ከጉባኤው ተመልሼ ቀጸልሁት። ባንድ ጊዜ ስለአጠናሁትም ወደ የኔታ ተመልሼ ሌላ ጉባኤ አነበብሁ። እሳቸውም “ምነው ልጄ የፊተኛውን አትደግመውም ወይ” ብለው ጠየቁኝ። “ስላጠናሁት ይበቃኛል ብዬ ነው” አልኳቸው። የሰጡኝም መልስ “አንተ ብታጠናው እኔ አላጠናሁትምና እንደገና ድገመው” የሚል ስለሆነ ደገምሁት። ይኸውም እንደ ዕውር ወልደ ጊዮርጊስ በትዕቢት እንዳልጠመድ ሊመክሩኝና ሊያሳስቡኝ ስለፈለጉ ነው።
ብላታ ዕውር ወልደ ጊዮርጊስን ሲያደንቁ፣ “አእምሮው እጅግ ብሩህ ስለሆነ ትምህርት አልመክትህ አለው። ... የሐዲሱን ንባብ ከሥር እስከ ጫፍ በቃሉ ይዞት ነበር። አንዱን ጉባኤ አንድ ጊዜ ብቻ ሰምቶ እስከ መያዝ ድረስ አስደናቂ የማጥናት ችሎታ ነበረው” ይሉናል። ስለራሳቸው ሲጽፉ፣ “ከዕውር ወልደ ጊዮርጊስ ደረጃ ባልደርስም ወደዚያው ለመጠጋት እሞክር ጀመር” ማለታቸው ትሕትና ነው። የሚያደንቁት ወልደ ጊዮርጊስ አንዱን ጉባኤ አንድ ጊዜ ሰምቶ እስከ መያዝ ድረስ የማጥናት ችሎታ ነበረው፤ የማያደንቁት መርስዔ ኀዘንም አስተማሪው ጉባኤውን አንድ ጊዜ ሲተረጒምለት ባንድ ጊዜ ስለሚያጠናው መምህሩ ቢፈቅዱለት ወደሚቀጥለው ጉባኤ ይሄድ ነበር። ብላታ ትምህርታቸውን ያካበቱት ከብዙ መምህራን ዘንድ ነው። በየትምህርት ቤታቸው አብረዋቸው ይማሩ ከነበሩት ተማሪዎች የብዙዎች ስም ይዘረዝሩና “የሌሎቹን ስም አላስታውስም” ሲሉ የሚገርመው ያንን ያህል ስም ማስታወሳቸው ነው።
ሊቃውንቱ (ዕውር ወልደ ጊዮርጊስን ጨምሮ) ትምህርታቸውን የሚያስፋፉት ለመሾም፣ ከሌላው ለመብለጥ ሲሆን የክቡርነታቸው ዓላማ ከዚያ የላቀ መሆኑን ከዚህ በታች ያለው ቃላቸው ይመሰክራል፤
እኔ (ከሀረር) ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ ያሰብሁት ስለ ሁለት ምክንያት ነበር። አንደኛ ከአስተማሪዬ ከመምህር ወልደ ጊዮርጊስ መቅድመ ወንጌልን ለመማርና ሐዲስን ለማጠናቀቅ ሲሆን፣ ሁለተኛም ወደ ቦሩ ሜዳ ለመሄድና ከመምህር አካለ ወልድ አረጋዊ መንፈሳዊን ለመማር ስለተመኘሁ ነበር። አረጋዊ መንፈሳዊን ለመማር የፈለግሁበትም ምክንያት “ይህ መጽሐፍ የሚማረው ጠፍቶ ሊጠፋ ነው” እየተባለ ይወራ ነበርና ትምህርቱን ለማስቀረት ስል ነው። በጐንደር ዘመነ መንግሥት ሕዝቅኤልና አቡሻክር የሚማረው ታጥቶ ትርጓሜው ጠፍቶ ቀረ እየተባለ ይነገር ነበረና አሁንም የአረጋዊ መንፈሳዊ ትርጒም ጠፍቶ እንዳይቀር ከልቤ አስቤበት ነበር።
ብላታ አልተናገሩትም እንጂ ትምህርቱን ለማስቀረት ያደረጉት ዋናው ነገር የጥንት አባቶቻችንን የክርስትና ሕይወት በመኖር ለዘመኑ ትውልድ ያሳዩት ቅድስና ነው። በክቡርነታቸው ዘመን ትምህርት ማለት ዕውቀት ማስተማሪያው ቀለሙ እንጂ፣ መልእክቱ መሆኑ ሲቀር ይታይ ነበር። ቀለሙን አጥርተው በማወቅ ስመጥር የነበሩ የዘመኑ ታላላቅ ሊቃውንት የዘመናችን ወጣት ልብስ እንደሚለዋውጥ ሚስት እያለዋወጡ የታላቅ ደብር አለቃ ለመሆን ጊዜያቸውን በደጅ ጥናት ያሳልፉት ነበር። ከእነዚህ ምሁራን ጋር እየዋሉ ያላንዳች ዳኅፅ በክርስትና ሕግ መኖርን ከምን አገኙት? ገድለ አባ ሊባኖስን የትምህርታቸው መጀመሪያ ካደረገላቸው ከልዑል እግዚአብሔር እንጂ ከመምህሮቻቸው ወይም ከወላጆቻቸው ያገኙት አይደለም።
ብላታ ስጦታቸውን “አንድ ለእናቱ” በሚያሰኝ ደረጃ እንደዚህ ለሀገራቸውና ለሃይማኖታቸው መቀደሳቸውን የሚያሳይ እነሆ ሌላ ምስክር እጠራለሁ። ቃሉ የሳቸው ሲሆን የሚጽፉት ግን እነጊዮርጊስ ወልደ ዓሚድ “ይቤ በዓለ መጽሐፍ” እንደሚሉት ራሳቸውን እንደ ሦስተኛ ሰው አድርገው “እሱ” እያሉ ነው፤
ንጉሥ እንዴት እንደሚነግሥ ለማየትና ሥነ ሥርዓቱን ለማጥናት ስለ ተመኘ፣ ትናንት በንግሡ ቀን የከልካዮቹን አርጩሜና ግፊያውን ታግሦ በአራዳ ጊዮርጊስና በየመንገዱ እየተዘዋወረ ሲመለከት ውሎ ነበር። በዛሬም ቀን ለግብር ከገባ ዘንድ በገበታ ተቀምጦ ከመብላት ይልቅ ቆሞ በመዘዋወር ሁናቴውን ለማየት ስለ መረጠ እንዲህ አደረገ፤ ኩታውን እንደ አጋፋሪዎች አሸንፍጦ አርጩሜ ያዘና ያስተናብር ጀመር። ለደንበኛው የአቦ አጋፋሪ ለደብተራ ወልደ መስቀል ዛሬ አጋፋሪ ሆኜ ለመዋል ፈልጌያለሁ ብሎ ምኞቱን ሲገልጥለት አንተ ከፈለግህ ምን ከፋኝ ብሎ ተስማማበትና በፈቃድ የሹመት ተካፋይ ሆነ። ይህ ሰው ሹመቱን ያገኘው በታሪክ ጸሐፊው አባት ነበርና እርሱን ለማክበር ሲል ፍላጎቱን ፈጸመለት።
እንግዲህ አጋፋሪ ሆኖ ወዲያና ወዲህ ማለት ጀመረ። የሌሎቹ አድባራት አጋፋሪዎችም በውነት የተሾመ መስሏቸው (ዱሮም ያውቁታልና) ጓደኛ አደረጉት፣ እርሱ ግን ሥራውን ለአጋፋሪ ወልደ መስቀል ለቀቅ አድርጎ እየተዘዋወረ ታሪኩን ለማየት ብቻ ተግቶ ዋለ።
ሌሎች ለግብዣው ምግብ ሲጋፉ፣ እየተዳጩ ሲሞቱም፣ ብላታ ሥነ ሥርዓቱን ለሚቀጥለው ትውልድ ለማሳለፍ በዚህ ሁኔታ እየተዘዋወሩ አንዳች ነገር ሳይጐድል ሁሉንም መዘገቡልን። ይኸንን ለማድረግ ምን መንፈስ አነሣሣቸው? ሥራው የጸሐፌ ትእዛዝ ነበር፤ ታዲያ ጸሐፌ ትእዛዙ በዚያ ጊዜ የት ነበር? ሥነ ሥርዓቱን እሳቸው ባይመዘግቡት የሆነውን በምን እናውቅ ነበር? እርግጥ ምዕራባውያን አንዳንድ ነገር ጽፈዋል፤ የሀገራችንን ታሪክ ከነሱ ከሆነ የምንማረው፣ እነሱ የሚጽፉት ራሳቸውን ማእከል እያደረጉ ነው። ለምሳሌ፣ በዚያ ጊዜ የእንግሊዝ ሱማሌላንድ ገዢ የነበረው ሰር ጄኦፍሪ አርቸር (Sir Geoffrey Archer) የመዘገበውን እንይ፤
ለአውሮፓውያን ኅብረተሰብ በተዘጋጀው በፊተኛው ተርታ የኢጣልያኑ ሚኒስትር ካውንት ኮሊ በኢትዮጵያ የዲፕሎማቶች ተቀዳሚ ስለሆነ መጀመሪያ ተቀመጠ። ሰውየው የኢጣልያ ንጉሥ ፈረሰኛ ስለነበረ በፈረሰኛ ሹም ልብሱ አሸብርቆ በኒሻንና በሽልማት ተሽቆጥቁጧል፣ ጽዱል ጥብጣብ (bright riband) አድርጎ የሚደነቅ ነበር። ከእሱ በታች በተከታታይ የእንግሊዝና የፈረንሳይ ሚኒስትሮች፣ ከነሱ ቀጥሎ የሩሲያ ጒዳይ ፈጻሚ ተቀመጡ። እኔ በተርታው ላይ አምስተኛ ነበርኩ። ከእኔ አንድ ቦታ ዝቅ ብሎ የፈረንሳይ ሱማሌላንድ እንደራሴ ገዢ ተቀመጠ። ንግሥተ ነገሥታቱ የቤተ ክርስቲያኑ ጸሎት ተፈጽሞ መምጣታቸው በእምቢልታና በሆታ እስኪሰማ ድረስ ቁጭ ብለን ስንጠብቅ ከወምበሬ ተነሥቼ የእንግሊዙን ሚኒስትር ለማነጋገር ስሄድ የጅቡቲው ገዢ እመር ብሎ ወምበሬን ወሰደብኝ። ካውንት ኮሊ አቅጣጫ በሚያሳይ ዓይንና እንደ አጋፋሪ የጎራዴውን መርገፍ እያቃጫለ ወዲያው መጣና ፈረንሳዩን ትከሻውን መታ መታ አድርጎ፣ “ሞንሴር፣ ተነሣና አንድ ቦታ ዝቅ ብለህ ከሚገባህ ቦታ ተቀመጥ” አለው።
ክቡር ብላታ መርስዔ ኀዘን ዕድሜያቸው እየጨመረ ሲሄዱ ምንም ለትምህርት ቢጓጉ በኑሮ ራሳቸውን መቻል እንዳለባቸው ይሰማቸው ጀመር። ዘመኑ ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኰንን አንደተናገሩት፣ “የጽፈት መኪና ከኤውሮፓ በገንዘ(ባቸው) አስመጥ(ተው) የመጻሕፍተ ብሉይንና የመጻሕፍተ ሐዲስን የመጻሕፍተ ሊቃውንትንና የመጻሕፍተ መነኮሳትን ንባባቸውን ከነትርጓሜያቸው ለማሳተም” የጀመሩበት ዘመን ስለሆነ ለዚያ ሥራ ካስፈለጉት አንዱ ሆኑ። አጋጣሚው ለብላታ የተማሩትን ለማጽናት ያላወቁትን ለማወቅ ዕድል ሰጥቷቸው፣ የሐዲሳት፣ የብሉያት፣ የሊቃውንት፣ የመጽሐፈ መነኮሳት ብቸኛ ተጠያቂ አደረጋቸው። ኅትመቱ በምን ዓይነት ጥንቃቄ እንደተፈጸመ ሲመዘግቡ እንዲህ ይላሉ፤
የትርጓሜውን ረቂቅ በጻፍሁ ጊዜ የሥራዬ እቅድ እንደሚከተለው ነበር። አንዱን ጉባኤ መጀመሪያ ከአስተማሪዬ ከመምህር ደስታ አስተረጒምና ብቻዬን ከቀጸልሁት በኋላ ወዲያው በእርሳስና በወረቀት የትርጓሜውን ረቂቅ አወጣለሁ። ቀጥሎም ያንኑ ጉባኤ እንደገና አስተርጒሜ ጌታ አለቃ ገብረ መድኅን ባሉበት እቀጽልና በፊት ያረቀቅሁትን እየመረመርሁ አስተካክዬ ንባቡንም በቦታው አስገብቼ የመጨረሻውን ረቂቅ እጽፋለሁ። ከዚህ በኋላ ይህን የጻፍሁትን ለአስተማሪዬ ለመምህር ደስታ አነብላቸውና እሳቸው “መልካም ነው፤ ልክ ነው” ሲሉኝ ለቁም ጸሐፊው እያስተላለፍሁለት ንባቡን በቀይ ትርጕሙን በጥቁር ቀለም እያስማማ ይጽፈዋል። አስተማሪዬ ያረሙት ቃል ሲኖርም አርሜ እሰጠዋለሁ። ይሁን እንጂ የእኔ ረቂቅ በአስተማሪዬ ዘንድ ሁልጊዜ ተቀባይነትን ያገኝ እንደ ነበረ አስታውሳለሁ።
እነዚያን መጻሕፍት ማን እንደጻፋቸው፣ ለምንስ ስሕተት እንደሌለባቸው አሁን ገባኝ።
ክቡር ብላታ መርስዔ ኀዘን የተወለዱት ኢትዮጵያ በምትፈልጋቸው ዘመን ነው። ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኰንን ትርጓሜ መጻሕፍቱን ለማሳተም ሐሳቡን ሲያቀርቡና ገንዘቡን ሲቸሩ የብላታ መርስዔ ኀዘን በቦታውና በዘመኑ መገኘት እንደተአምር የሚቈጠር ለመሆኑ ከላይ የተጠቀሰው ጥቅስ ያሳያል። አልጋ ወራሽ መጻሕፍቱን ለማሳተም ሲያስቡ መጀመሪያ ሊቃውንቱን ማስፈለግ ነበረባቸው። ልብ ያለው የለም እንጂ ልዑሉ ያገኙት በመጀመሪያ ደረጃ ብላታን ነበር ማለት ይቻላል። የኛ ሊቃውንት እንደነ ዕውር ወልደ ጊዮርጊስ በቃል መማርና ማስተማር እንጂ ከመጻፍ ጋር ብዙም ስለማይተዋወቁ እንደ ብላታ ያሉ ብዙ ሌላ ሰው አላገኙም።
ለምሳሌ፣ የብላታ የመጻሕፍተ መነኮሳት አስተማሪ መምህር ደስታ ለሥራው ከተጠሩት አንዱ ነበሩ። አልጋ ወራሽ ከመርጦ ያስመጧቸው አስተማሪያቸው መምህር አካለ ወልድ የጀመሩትንና ሳይጨርሱት ሞት ያቆመውን የአረጋዊ መንፈሳዊን ትርጓሜ እሳቸው እንዲጨርሱት ነበር። መምህር ደስታ አልጋ ወራሽ ፊት ሲቀርቡ የሰጡት መልስ ሊቃውንታችንን በመሃይምነት የሚያሳማቸው ቢሆንም የተገኙት ብላታ ብቻ መሆናቸውን በይበልጥ ያሳያል፤ “ትርጓሜውን መተርጐምና ማስተማር እችላለሁ፤ ነገር ግን እኔ እየተረጐምሁ እጽፋለሁ ያልሁ እንደሆነ ያስቸግረኛልና እኔ እየተረጐምሁለት ተምሮ የሚጽፍ ደቀ መዝሙር ቢሰጠኝ እወዳለሁ” የሚል ነበር። ሌላ ሊቅ ይወለድ ማለታቸው ነው። ያ ሊቅ ክቡር ብላታ መርስዔ ኀዘን ነበሩ። ትርጒሙ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣልን የአበው ነው። ለታተመው ባለቤት ካስፈለገ ግን የአረጋዊ መንፈሳዊ፣ የመቅድመ ወንጌል፣ የሰባቱ ኪዳናት ትርጒምና ለሌሎቹ እርማት ክቡር ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ ሲሆኑ ለሌሎቹ መጻሕፍት አሁን ብላታ ማን እንደነበሩ ስማቸውን የነገሩን ሊቃውንት ናቸው። ከማን ያልተማረ ኖሮ፣ “ከኔ ተምረህ አሳተምከው” ሊላቸው ይችላል? አልጋ ወራሽ ልዑል ራስ ተፈሪም ለሚደነቀው ትጋታቸውና ለለጋሽነታቸው ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። ሥራውን የሠሩት እነማን እንደነበሩ ስማቸው እንዲነገር አለማድረጋቸው ግን የሥራው ትክለኛ ሆነው እነ ብላታን በቶፍነት ያስሠሯቸው መስሎባቸዋል። ብላታ ሁሉን ነገር በቅን ስለሚያዩት፣ ስማቸው ያልተጻፈው ሥራው የመንግሥት ስለሆነ ነው የተባለውን ምክንያት ተቀብለውታል። ሥራው አልጋ ወራሽ በገንዘቤ ተሠራ ስላሉ የሳቸው ነው እንጂ የመንግሥት አይደለም፣ የመንግሥት ቢሆንም መንግሥትን በቅን ላገለገለ መታሰቢያ ይቆምለታል እንጂ አይጨቆንም።
ብላታ የተገኙበት ዘመን ኢትዮጵያ ከምዕራቡ ዓለም በይበልጥ የተገናኘችበት ዘመን ነበር። የኢትዮጵያ ባለሥልጣኖች (መጀመሪያ ልዑል ራስ መኰንን በኋላ ልዑል ራስ ተፈሪ) በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የውጪውን ሀገር ያዩበትና ኢትዮጵያ በዘመኑ ሥልጣኔ ወደኋላ የቀረችው የነሱን ሥርዓተ ትምህርት ባለማግኘቷ መሆኑ የታመነበት ዘመን ነበር። በዚህ ሰዓት ኢትዮጵያዊው ትምህርትና ባህል የምዕራቡን ዕውቀት አስተናጋጅ መሆን ሲገባው መጤው ትምህርትና ባህል “አልጋ ነጣቂ” ሊሆን አሰፈሰፈ። ሌሎች ቁጭታቸውን በመግለጽ ሲወስኑ፣ ክቡር ብላታ መርስዔ ኀዘን ችሎታቸውና ቅናታቸው ጋሻ ሆነውላቸው የተቻላቸውን ያህል መክተው ያዙት። ቋንቋውን በመማርና ከተማረ ጋር በመሆን ዕውቀቱን ውበት ባለው አማርኛ አስተናገዱት። ባህላችንን በመከተል የዘመኑን ታሪክ መመዝገብ የሚጀምሩት ዘመኑ የባተበትን ቀን በመመዝገብ ነው። እንደ “ተክሉ” (ክቡር ብላታ መርስዔ ኀዘን አቶ ተክለ ጻድቅ መኲሪያን “ተክሉ” ነበር የሚሏቸው) የታሪክ መጻሕፍትን መርምረዋቸዋል፤ በዚያ ላይ ውሏቸው ከሊቃውንቱ ጋር ስለነበረ በቃል ሲወርድ ሲዋረድ እሳቸው ዘንድ የደረሰውንም ስለሚያውቁት የሚጽፉት ሁሉ ትምህርት በትምህርት ነው።
የአማርኛ ሰዋስው መጻሕፍታቸው የምዕራቡን ምርምር በሀገራዊ ሥርዓት ለማስተናገዳቸው ጉልሕ ምሳሌ ነው። “በአማርኛ ስምንት የንግግር ክፍሎች አሉ” ብለው ሲያስተምሩን የአማርኛን ሰዋስው ከአባቶቻቸው ሊቃውንት በወረሱት የግዕዝ ሰዋስው ስልትና በምዕራባውያን ምርምር መመገባቸው ነው። ሰዋስው እንደቊጥር ሎጂክ መሆኑን ያልተገነዘቡ ሰዎች የእንግሊዝኛን ሰዋስው ለአማርኛ እንዳወረሱ ይቈጥሯቸዋል። ሰዋስው ሀገር የለውም፤ ሰዋስው ማለት “መሰላል” ማለት ነው፤ ለምን መሰላል እንደተባለ የሚያውቁት ያበደሩን ዐረቢኛ የሚናገሩ ቅብጢዎች ናቸው። አሁን ደግሞ ዓለም የሚከተለው (የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም) የአሜሪካዊውን የናሆም ቾምስኪን ሰዋስው ሆኗል።
ብላታ በሥራቸው ላይ እያሉ የውጭ አገር ትምህርትም ለመማር፣ በ1913 ዓ.ም. የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ተማሪ ሆነው ነበር። መምህራቸው አለቃ ገብረ መድኅን ለጒዳይ ከሄዱበት ሲመለሱ ብላታ ትምህርት ቤት መግባታቸውን ሰምተው እያዘኑ የትርጓሜውን ሥራ ብቻ እንዲከታተሉ አደረጓቸው። ብላታ ጠባያቸው በሆነ ቅን አስተሳሰብ ተግሣጹን እንዲህ ሲሉ ተቀብለውታል፤ “ጌታ አለቃ ገብረ መድኅን ይህን ማድረጋቸው እኔን ለመጥቀም እንጂ ለክፋት እንደላደረጉት ሕሊናዬ ስላወቀው አላዘንሁባቸውም።” ሆኖም የብላታ እንግሊዝኛ ለሚፈልጉት ሥራ እንዳበቃቸው ከእንግሊዝኛ የተረጐሟቸው መጻሕፍት፣ የመለሱት ሰዋስው፣ የማርቆስ ዳዉድን የመጸሐፈ ቅዳሴ እንግሊዝኛ ትርጒም ያረሙት ያሳያሉ።
ክቡር ብላታ መርስዔ ኀዘን እንደ ትልቁ አጎታቸው እንደ አለቃ ገብረ ክርስቶስ ስለጵጵስና ጒዳይ ግብጽ ሄደው ነበር። ግን በሁለቱ መካከል ታላቅ ልዩነት አለ፤ አለቃ ገብረ ክርስቶስ ግብጽ የወረዱት ጳጳሳት ለማምጣት ስለነበረ የሰጧቸውን ይዘው ተመልሰዋል፤ ብላታ የሄዱት ራሱን የጵጵስናውን ሥልጣን ለማምጣት ስለነበረ የሰጧቸውን ሳይሆን የፈለጉትን ይዘው በድል አድራጊነት ገብተዋል። በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጳጳስ ለማስመጣት ወደግብጽ ልኡካን መላክ የተለመደና የተደጋገመ ነበር፤ ከልኡካኑ ውስጥ አንዳቸውም የሆነውን በጽሑፍ አላቆዩልንም። እንደነ ዕውር ወልደ ጊዮርጊስና መምህር ደስታ በቃል መማርና ማስተማር እንጂ ከመጻፍ ጋር ብዙም ስለማይተዋወቁና የዘመናቸው መርስዔ ኀዘኖች አብረዋቸው ስላልነበሩ ታሪካችን መና ቀርቷል። ብላታ በነበሩበት ተልእኮና ውጤቱ ግን በብላታ ብዕር በዝርዝር ተመዝግቦ ከስማቸው ጋር ለዘለዓለም ነባር ሆኗል።
ብላታ ስለልጅ ኢያሱ ይባል ከነበረው ብዙውን ጽፈውልናል። ነገር ግን የሰውን ሐሳብ ሁልጊዜ በበጎ ዓይን ስለሚያዩ መስፍኑ ለኢትዮጵያ አስተዳደር አስጊ መሆናቸውን ሌሎቹ የሚፈሩትን ያህል አልፈሩም። ሌሎች እንደጥፋት ያዩባቸውን ከአንዳንዱ በቀር ሌላውን ብላታ አላዩባቸውም። ልጅ ኢያሱ እርግጥ የክርስቲያኑም የእስላሙም ገዢ ነበሩ። ነገር ግን “ሃይማኖት የግል ነው፤ ሀገር ግን የጋራ ነች” የሚባለው አስተያየት ባልተሰማበትና አቡኑና እጨጌው የገዢው ክፍል በነበሩበት ዘመን “የሁላችሁም ነኝ” ለማለት የሁሉንም ሃይማኖት መያዝ ይቻል ነበር ወይ? ልጅ ኢያሱ ክርስቲያንም እስላምም፣ ከዚያም አልፎ ልዑል ራስ እምሩ እንደመዘገቡት፣ አምላክ-አልባም ሲሆኑ ይታያሉ። ክርስቲያን ሆነው ከመስጊድ ገብተው እንደሙስሊሞቹ የሚጸልዩት እንኳን በበጎ ዓይን ሊታይ ይችላል። ግን በሄዱበት ቦታ ሁሉ የሙስሊም ባላባቶች ልጆች ሲያገኙ ያገቧቸው የነበረው ለምንድን ነው? የክርስትናን ሕግ ለደስታቸው መጣሳቸው ነው ወይስ መስለማቸው ወይስ ሃይማኖት-አልባ መሆናቸው ኖሯል? የዚያ ጊዜይቱ ኢትዮጵያ መሪ ሆነው ይኸንን ማድረጋቸው፣ በዚያ ላይ ሀረር ተቀምጠው ከሙስሊሞች ጋር እየዶለቱ አዲስ አበባ ላይ ከመኳንንቱና ከካህናቱ ጋር የሚዶልቱትን ልዑል ደጃዝማች ተፈሪን ከሀረርና ከአዲስ አበባ ለማባረር መሞከር ማንም የበሰለ ፖለቲከኛ የማያደርገው ነው። መስፍኑ በተያዙ ጊዜ “ልጅነትን እግዚአብሔር ይማርሽ በሏት” አሉ የተባለው እውነት ከሆነ፣ ጸጸታቸውን የገለጹት በሚገባ አነጋገር ነው። ባለማወቅ አልጋቸውን አጡ፤ ኢትዮጵያም በሰገሌና በሚቀጥሉት ጦርነቶች ስፍር ቊጥር የሌላቸውን ልጆቿን አጣች።
ብላታ በፈቃዳቸው የገቡበትን ግዴታ በሌላ አጋጣሚ፣ “እንግዲህ አንባቢ ... የፈቀደውን ያትት፤ የኔ ሥራ የሰማሁትን ነገር በሰማሁት ዓይነት ማቅረብ ነው” ብለው ሊጠቀሱ በሚገቡ ቃላት ደምድመውታል። ቅሬታዬን አንሥቻለሁ።
ጌታቸው ኃይሌ