Book 1 Blurb 3 Bishop

ክቡር ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ፥ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብዙ ታላላቅ ውለታ አስመዝግበው ያለፉ፥ ከፍተኛ የትምህርትና የባህል መሪ መሆናቸውን የማያውቅ የሚኖር አይመስለኝም። በተለይ፤ የተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት ሲቋቋም፥ የመጀመሪያው የግእዝና የአማርኛ አስተማሪ በነበሩበት ጊዜ ባዘጋጁት የአማርኛ ሰዋስው ያልተጠቀመ ተማሪ አይገኝም። በዚህ ምክንያት፥ የሳቸው ስምና ዝና፥ ከልጅነታችን ጀምሮ በአእምሯችን ተቀርፆ ይኖራል። በቅርቡ፥ በልጃቸው በአቶ አምኃ ጠንቃቃ አዘጋጅነት፥ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያሳተመላቸው፥ የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ: የዘመን ታሪክ ትዝታዬ፥ ካየሁትና ከሰማሁት 1896-1922 የተሰኘው መጽሐፋቸው፥ ለሁልጊዜ የሚቆይ ትልቅ ሐውልት ሆኖላቸዋል። አሁን ደግሞ፥ ይህንን፥ ትዝታዬ፥ ስለራሴ የማስታውሰው በሚል ርእስ የጻፉትን፥ የግል ሕይወት ታሪካቸውን፥ ይኸው የተባረከ ልጃቸው በጥራት አዘጋጅቶ አቅርቦልናል።
ይህን መጽሐፋቸውን በእውነቱ፥ ከራሳቸውም የሕይወት ታሪክ ባሻገር፥ ባጠቃላይ የኢትዮጵያን ጥንታዊ የትምህርትና የልጅ አስተዳደግ ሥነ ሥርዓት በዝርዝር እንደሚያስተምር ትልቅ መዝገብ ልናየው እንችላለን። የንባብ ትምህርት፥ በጅሩ ገጠር በሚገኝ ያያቶቻቸው ቤተ ክርስቲያን፤ ዜማ ደግሞ፥ በድጓ መምህርነታቸው በጣም ይከበሩ በነበሩት አባታቸው፥ በአለቃ ወልደ ቂርቆስ ቀጥተኛ ቁጥጥር ሥር፤ ቅኔ፥ ጻድቁ አቡነ ዜና ማርቆስ ባቋቋሙት የደብረ ብሥራት ገዳም፤ እንደዚሁም የመጻሕፍት ትርጓሜ፥ ዝናቸው እስከ ቤተ መንግሥት ድረስ ከታወቀላቸው ታላላቅ መምህራን፥ የተሟላ ሥልጠና አግኘተዋል። እንደዚህ በየደረጃው ያለፉበትን የትምህርትና የመልካም አስተዳደግ መንገድ ብቻ ሳይሆን፥ በጊዜው ስለነበሩ የማህበራዊና ጠቅላላ የሀገር ጉዳዮችም በየስፍራው ይጠቃቅሳሉ። ይልቁንም፥ በሌላ ቦታ የማይገኝ፥ ስለ ኢትዮጵያ ጥንታዊ የትምህርት ዓይነቶችና ስለይዘታቸው የተጣራ ዝርዝር መግለጫ በዚህ መጽሐፍ መጨረሻ ላይ ቀርቦልናል።
ደራሲው፥ በብዙ ነገሮች የመጀመሪያ የመሆን እድል አጋጥሟቸዋል! በተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት የመጀመሪያው የአማርኛና የግእዝ ቋንቋ መምህር ነበሩ። እንደዚሁም፥ በጅጅጋ ከተማ፥ በራስ መኰንን ስም ተሰይሞ የነበረውን የመጀመሪያውን ትምህርት ቤት አቋቁመው፥ የመጀመሪያው ዲሬክተር ሆኖ የመምራት እድል ያገኙት እሳቸው ናቸው።
ይህ የትዝታ መጽሐፍ፥ 1922 ዓም ላይ ነው የሚቆመው። በመሆኑም የደራሲው የራሳቸው፥ ከ፵ ዓመት የሚበልጥ የሕይወት ታሪካቸው እዚህ አልተሸፈነም ማለት ነው። ነገር ግን፥ በነዚህ አያሌ ዓመታት ውስጥ ነበር፥ እስከ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ተፍጻሜት ድረስ፥ ለአገራቸው ከፍተኛ አገልግሎት ያበረከቱት! በተለይ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከግብፁ የእስክንድርያ ፕትርክና ነፃነቷን እንድታገኝ በተደረገው ዘዲያማ ዲፕሎማሲ፤ በብሔራዊው ፓርላማ ሥራ እድገትና፥ በተለያዩ የተምህርትና የባህል ድርጅቶች ዓይነተኛ የአመራር አስተዋፅኦ ያበረከቱት በነዚሁ ዓመታት ነበር! በውነቱ ክቡር ብላታ መርስዔ ኃዘን፥ የነዚህንም ዓመታት ታሪክ ቢሸፍኑልን ኖሮ፥ በቅርብ ታሪካዊ ዘገባ እጅግ በጣም የተራቆተውን የንጉሠ ነገሥቱን ውስጣዊ ህልውና ታሪክም ጭምር፥ እግረ መንገዳቸውን በሚገባ ሳያብራሩልን አይቀሩም ነበር!
ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት