Book 5 Blurb 1 Baye

 
ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ ለኢትዮጵያ የቋንቋ ትምህርት ፈር ቀዳጅ ናቸው። እስከ 66ቱ ዐብዮት ዋዜማ ድረስ በነበረው የትምህርት ሥርዓት ያለፈ ሁሉ እሳቸው በጻፉት የአማርኛ ሰዋስው ያልተማረና ወይም ያላስተማረ የለም ለማለት ይቻላል። እኔም በመጽሐፉ ከተማሩትና በኋላም እሳቸውና መሰሎቻቸው ካቆሙበት በመነሣት የአማርኛ ሰዋስውን ከዘመኑ የሥነ ልሳን ሳይንስ አኳያ ለመጻፍና ለማስተማር ከበቁት መካከል አንዱ ለመሆን ችያለሁ። የእሳቸውን የሰዋስው መጽሐፍ የሚያነብ ሁሉ ስለ ቃላት አገባብ፣ ሐረግ አመሠራረት እና አረፍተ ነገር አወቃቀር ብቻ ሳይሆን፣ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ስለ ዕፀዋት፣ እንስሳትና ማዕደናት ዓይነትና ባህሪ መሠረታዊ ዕውቀት ያገኛል። ለየመልመጃው መነሻ እንዲሆኑ አስበው ያቀረቧቸው ምንባቦችም ይህን ዓላማ መሠረት አድርገው የተመረጡና የተዘጋጁ ናቸው። የቋንቋ አጠቃቀማቸውም አንባቢውን ስለ ድርሰት አጻጻፍ ስልት እንዲያውቅና ስለ ሥነ ጽሑፍም መሠረታዊ ግንዛቤ እንዲያገኝ የሚያደርጉ ናቸው። በዚህም ብላታ ለሀገራችን የሥነ ጽሑፍ እድገት አስተዋጽዖ አድርገዋል።
ከትምህርቱ ባለፈም ብላታ መርስዔ ኀዘን ራሳቸው የደረሱትን፣ ከውጭ የተረጎሙትን፣ የዘመን ትውስታቸውን፣ በግንባር ያዩትንና የሰሙትን ሁሉ በጽሑፍ አቅርበውልናል። ከውጭ የሔሮደቱስ ከውስጥ ደግሞ የአባ ባህሬይ የታረክ ጽሑፎች ከተተረጎሙት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ከትውሰታውም ሆነ ከትዝታው በጽሑፍ ያቆዩልን ዕወቀት በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ሲጠቀስ የሚኖር ይመስለኛል።
ባየይማም
የሥነልሳንፕሮፌሰር
አዲሰአበባዩኒቨርሲቲ