መቅድም

ክቡር ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ በ1891 ዓ.ም. ተወልደው ከሕፃንነታቸው ጀምሮ የመዝገበ ድጓ መምህር በነበሩት አባታቸው አለቃ ወልደ ቂርቆስ የቅርብ ክትትል በቤተ ክህነት ትምህርት ተኮትኩተው አድገዋል። ዕድሜያቸው ለአካለ መጠን ደርሶ ወደ ሥራ መስክ ሲሠማሩ እጅግ ስመጥር ከነበሩ እንደ አለቃ ገብረ መድኅን፣ መምህር ደስታ (በኋላ አቡነ አብርሃም) ከመሳሰሉ ሊቃውንት በተማሪነትም፣ በጸሐፊነትም ሰፊ ዕውቀትን ቀስመዋል።
የብርሃንና ሰላም ጋዜጣ በ1917 ዓ.ም. ሲመሠረት የድርጅቱ ዋና ጸሐፊና በልዩ ልዩ አርዕስት ጥናቶች እያዘጋጁ በማሳተም ተሳትፈዋል። የተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት ሲቋቋም የአማርኛ መምህር ሁነው በማገልገል እያሉ የአማርኛ ሰዋስው አዘጋጅተዋል። በጅጅጋ የትምህርት ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆን አገልግለዋል። የኢጣልያ ወረራ ዘመን አክትሞ የኢትዮጵያ ነፃነት ከተመለሰም በኋላ በጽሕፈት ሚኒስቴር የታሪክና የቤተ መንግሥት ዜና ማዘጋጃ ክፍል አላፊ ሁነው በመሥራት በርካታ የታሪክ ሰነዶች ለመመርመር ሰፊ ዕድል አጋጥሟቸዋል።
ክቡር ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ “የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ካየሁትና ከሰማሁት” “የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በአቤቶ ኢያሱ ዘመነ መንግሥት ካየሁትና ከሰማሁት” “የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥት ካየሁትና ከሰማሁት” በሚል አርዕስት ባበረከቷቸው ጽሑፎች ላይ በሕይወታቸው ያከማቹት ዓለማዊና መንፈሳዊ ዕውቀት ይንጸባረቃል። የዘመኑን ታሪክ በያመቱ ከፋፍለው በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ቁልጭ አድርገው ለማሳየት ጥረዋል።
በተጠቀሱት ጽሑፎች ላይ አብዛኛው የተመዘገበው ራሳቸው ተካፋይ ሁነው እንዳሉትም “ያዩትን የሰሙትን” ትዝታቸውን ነው። አልፎ አልፎ ደግሞ ስለ አንዳንድ ልዩ ሁኔታዎች ከታመነ ምንጭ ትክክለኛውን ሁኔታ ለመረዳት ሞክረዋል።
የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ካየሁትና ከሰማሁት በሚል ስያሜ በጻፉት ላይ፤
ራስ መኰንን ለእንግሊዝ ንጉሥ ኤድዋርድ ሰባተኛው ንግሥ በዓል ኢትዮጵያን ወክለው እንዲገኙ ተልከው በ1894 ዓ.ም. ወደ እንግሊዝ አገር ባደረጉት ጒዞ የነበረውን ሁናቴ አብረዋቸው ከሄዱት ከጸሐፌ ትዕዛዝ ኃይሌ ወልደ ሩፌ የተነገራቸውን ዘግበዋል።
የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በአቤቶ ኢያሱ ዘመነ መንግሥት ካየሁትና ከሰማሁት በሚል አርዕስት በጻፉት ላይ፤
ወደ ነምሳ (ኦስትሪያ) ሄዶ ስለ ነበረው የልዑካን ቡድን፣ የመልክተኞች መሪ ሁነው ከሄዱት ከደጃዝማች በላይ አሊ የተነገራቸውን፤ “ጥርምቡሌዎች” በመባል የታወቁት ዘበኞች ከኤርትራና ሱማሌ አመጣጥ፣ ከነሱ አንዱ ከሆኑት አቶ መንገሻ ገዛኸኝ ጠይቀው የተረዱትን፤
አቤቶ ኢያሱ ከአዲስ አበባ ለመጨረሻ ጊዜ እንዴት ወደ ሐረር እንደሄዱ የምክሩ ተካፋይና የአቤቶ ኢያሱ ባለሟል የነበሩት ነጋድራስ ተሰማ እሸቴን ጠይቀው እሳቸው የነገሩዋቸውን ገጽ 132 ላይ ዘግበዋል።
እንዲሁም የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥት ካየሁትና ከሰማሁት በተሰኘው ጽሑፋቸው፤
ንጉሥ ሚካኤል ራስ አባተ ቧያለው ታስረው ከነበሩበት ከልጎት አምጥተው ደሴ እሳቸው ዘንድ በክብር አኑረዋቸው እንደነበር፣ የመንግሥት ለውጥ አዲስ አበባ ላይ መደረጉን ንጉሥ ሚካኤል ሲሰሙ ሊቀ መኳስ አበጋዝን ራስ አባተን እንዲያስሩ ማዘዛቸውን፣ ሊቀ መኳስ አበጋዝ ራስ አባተን የመንግሥት ለውጥ በመኖሩ እንዲታሰሩ ንጉሥ አዘዋል ሲሏቸው፤ “ሀብተ ጊዮርጊስ እኔን እስከ መቃብር ሳያደርስ አይተወኝም ቀድሞ (በ1904 ዓ.ም.) አሳሰረኝ፣ አሁን ደግሞ እኔን ለማስገደል ይህን ሥራ ሠራ” ማለታቸውን፣ ሊቀ መኳስ አበጋዝ ነገሩኝ ብለው ደጃዝማች ጎበና ዓመዴ የነገሩዋቸውን ዘግበዋል።
አቤቶ ኢያሱ አዳል በረሃ ሳሉ ተከታዮቻቸው ከፈረንሳይ ወይም ከኢጣልያ መንግሥት መሣሪያ ለማግኘት ብንላላክ ይሻላል ቢሏቸው፤
“እኔ ወደ ፈረንጆች ተጠግቼ ለአንዱ ብፈርም አገሬን መሸጤ ነው። ብዙ ዘመን ተከብራና ተፈርታ የኖረችውንም የኢትዮጵያ መንግሥት ማዋረዴ ነው። አሁን መንግሥቴን የያዙት እኅቴና ወንድሜ ናቸው እንጂ ባዕድ አልቀማኝም። አባቴ ንጉሥ ሚካኤልም ወደ ሸዋ መዝመታቸውን ሰምቻለሁና እኛም እንደርስባቸዋለን ስለዚህ ተስፋ አትቁሩጡ።” አሏቸው ብሎ አብሮ የነበረ አቶ ደስታ ወርቄ ነገረኝ ሲሉ በገጽ 166 ላይ ዘግበዋል። ዋቢ የሆነው ምንጫቸውን መግለጽ በጣሙን የሚያስመሰግን ነው።
በሦስቱም ጽሑፎች የቤተ መንግሥቱና የቤተ ክህነቱ ወግና ሥርዓት እንደ ተቀጸል ጽጌና መስቀል ያሉ በዓላት ሲከበሩ የተሰበከውን ምስባክ፣ ተረኛ እንዲሆን የተመደበው ደብር ያሰማውን ወረብ፣ የታየውን የወታደር ሰልፍ፣ በተለይ በንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ ሥርዓተ ንግሥ፣ እንዲሁም በራስ ወልደ ጊዮርጊስና በራስ ተፈሪ ንግሥ በዓል የታየውን፣ የኢትዮጵያ መምህራን ለመጀመሪያ ጊዜ ሢመተ ጵጵስና ተቀብለው ከግብጽ ሲመለሱ እንዲሁም የእስክንድሪያ ፓትርያርክ ኢትዮጵያን ሲጎበኙ የተደረገላቸውን አቀባበል በጠራ ቋንቋ አጣፍጠው አቅርበዋል።
በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን የነበሩት ታዋቂ መኳንንቶች የስም ዝርዝር፣ በየጊዜው የተደረጉትን ሹም ሽሮች፣ በያመቱ ከሞቱት ታላላቅ መኳንንት ወይዛዝርት እና ታዋቂ ሰዎች እየመረጡ ዘግበዋል። ያንዳንዱን ታዋቂ ሰው የሕይወት ታሪክም አስፋፍተው በመጻፍ በሰፊው የማይታወቁ ነገሮችን ገልጸዋል።
በአስተዳደር፣ በዳኝነት የተደረገው መሻሻል፣ በልማት መስክ ዳግማዊ ምኒልክ በ1896 ዓ.ም. የሰርኪስን ባቡር ካስመጡበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ ዕረፍት 1922 ዓ.ም. ድረስ፣ እንደ መንገድ ሥራ፣ የምድር ባቡር አገልግሎት መስፋፋት፣ የአውሮፕላን መምጣት፣ የግብጽ ባንክ ቅርንጫፍ የነበረው የአቢሲንያ ባንክ ስምምነት ተደርሶ ብሔራዊ እንዲሆን መደረጉን፣ የማተሚያ ቤት መስፋፋት፣ በምርጥ ሊቃውንት መንፋሳዊ መጻሕፍት ተተርጒመው ለሕዝብ እንዲዳረሱ መደረጉን ፣ የመንፈሳዊ ጉባኤ መቋቋሙን፣ የባሮች ነፃነት ደንብ መታወጁን፣ ዘመናዊ ትምህርት ቤት መስፋፋቱን፣ ተማሪዎች ለከፍተኛ ትምህርት ወደ መካከለኛው ምሥራቅ፣ አውሮፓና አሜሪካ መላካቸውንና ይህን የመሳሰሉትን ሁሉ ያካተተ ገለጻ አቅርበዋል።
የማኅበረሰብ ሁኔታዎችንም በተመለከተም አዶ ከበሬ እንዴት እንደ ተስፋፋ፣ በእጣን ታጅቦ ቡና የመጠጣት ባህል መቼና እንዴት በከተማ እንደተለመደ፣ የሙጀሌ ፣ የጣጣቴ፣ የኅዳር በሽታ አመጣጥ፣ ምክንያቱ ሳይታወቅ በ1911 ዓ.ም. ከግንቦት 11 ቀን እስከ ግንቦት 21 ቀን በአዲስ አበባ ላይ የታየው የመዓት ቃጠሎ የመሳሰሉትን በመግለጽ የታሪኩን አድማስ ማስፋፋታቸው ከተለመደው ታሪከ ነገሥት አጻጻፍ የተለዬ ያደርገዋል።
ስለ አቤቶ ኢያሱ ዘመን ጽሑፋቸው ላይ በርከት ያሉ ክፍተቶች ይስተዋላሉ። ይህ የሆነበትም ምክንያት በከፊል የአቤቶ ኢያሱ የሥልጣን ዘመን ራስ ቢትወደድ ተሰማ ናደው ከሞቱበት ሚያዝያ 3 ቀን 1903 ዓ.ም. ጀምሮ ዳግማዊ ምኒልክ እስከ ዐረፉበት ታኅሣሥ 3 ቀን 1906 ዓ.ም. ድረስ ያለው “የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት” ብለው በጻፉት ውስጥ ስለተካተተ ነው።
ክቡር ብላታ መርስዔ ኀዘንን ለረጅም ዘመን በልዩ ልዩ ሥራ በተለይም የኮዲፊኬሽን ኮሚቴ አባል ሆኜ የሕግጋት ረቂቅ በሚዘጋጅበት ወቅት፣ ቀጥሎም የፍርድ ሚኒስትር ሆኜ ሳገለግል በቅርብ ላውቃቸውና በልዩ ልዩ ዘርፍ ሰፊና ጥልቅ ዕውቀታቸውን ለማድነቅ ታድያለሁ።
ባጠቃላይ መጽሐፉ ከ1896 ዓ.ም. እስከ 1922 ዓ.ም. ያለውን ዘመን የታሪክ መረጃዎች የመዘገበ በቋሚ ምስክርነት የቀረበ በመሆኑ ለቈየው፣ ላሁኑና ለመጪው ትውልድ ግንዛቤና ትምህርት እንደሚሰጥ አምናለሁ።
ልጃቸው አቶ አምኃ መርስዔ ኀዘን በብዙ ድካም የግርጌ ማስታወሻዎችንና በርካታ ፎተግራፎችን ጨምሮ “የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ” በሚል ስያሜ አቀናብሮ ያባቱን ድካም ከኅትመት በማብቃቱ ከአድናቆት ጋር ከፍ ያለ ደስታ ይሰማኛል።
ዘውዴ ገብረ ሥላሴ