ማስተዋወቂያ

ግለ-ታሪክ ያንድ ግለሰብ ሕይወት ትረካ ነው። ይህ ማለት ደግሞ ተራኪው በሕይወት ዘመኑ የወጣ የወረደበትን ሁሉ ይናገራል ማለት እንዳይደለ ግልጽ ነው። ስለዚህ መምረጥ አለበት ማለት ነው። ከመረጠ ደግሞ ሆነ ብሎም ይሁን ሳያውቅ የሚገለገልባቸው መስፈርቶች ይኖሩታል። አንዱ መስፈርት ግለታሪኩን ለመጻፍ ከወሰነበት መሠረታዊ ዓላማ ይመነጫል። በፈቃዱ በራሱ ላይ የሚጥለው ማእቀብ ወይም ግላዊ ስንሰራም ይኖራል። ለባህልና ወጉ ያለው ታማኝነት “እኔም፥ ያደግሁበትና የኖርኩበት ባህሌም በአደባባይ ለመናገር የማንፈቅደው አለ!” ብሎ ከጽሑፉ የሚያስወግዳቸውም ይኖራሉ። “ይሄ-ይሄ አይጠቅምም!” ብሎ ከጽሑፉ የሚያስወግዳቸውም ይኖራሉ። በሚጽፍበት ጊዜ ያልመጣለት፥ ያላስታወሰው ቁምነገርም ሳይጽፍ የሚቀርበት ጊዜም አይኖርም አይባልም። እንዲህ እንዲህ ያሉትንና እነርሱን የመሳሰሉ መላ ምቶችን ከተራኪው ጽሑፎችና ከሌሎች ምንጮች የሚያገኛቸውን መረጃዎች አጥንቶ ዕውቀታችንን ይበልጥ የሚያዳብር ተመራማሪ ይመጣል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። እስከዚያ፥ ትዝታዬ ስለ ራሴ የማስታውሰው የተባለውን የመርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ መጽሐፍ ሳጣጥም ከቀሰምኩት መጽሐፉን ለአንባብያን ለማስተዋወቅ ይጠቅማሉ ያልኳቸውን አንዳንድ ነጥቦች ከዚህ በታች አቀርባለሁ። የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ - የዘመን ታሪክ ትዝታዬ - ካየሁትና ከሰማሁት፥ 1896 - 1922 (1999 ዓ.ም.) ስለተባለው መጽሐፋቸውም አልፎ አልፎ አነሳለሁ። ይህንን የማደርገው፥ በአጋጣሚው በመጠቀም ሁለቱ መጻሕፍት ለምርምር ያላቸውን አስተዋጽኦ ለማጉላት ስል ነው።
ጥሩ ግለ-ታሪክ፥ ተመራማሪዎች ነጣጥለው የሚያጠኗቸውን ቁም ነገሮች አዋህዶ፥ በመሀከላቸው ያለውን መስተጋብር ጠብቆ፥ የሕይወትን ቡራቡሬ መልክ ይስላል። ለምሳሌ፥ የመርስዔ ኀዘን ትዝታዬ . . . ስለ ቤተሰብ ሲተርክ አኗኗሩን፥ የልጅ አስተዳደጉን፥ የሥራውን ዓይነትና ጥረቱን፥ ሕመምና ጤናውን ፥ መድኃኒትና መርዙን ወዘተ. በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ እያስተሳሰረ በየቦታው ያቀርባል። ይህንን በማድረጉም፥ የጸሐፊውን ማንነት፥ ማለትም የሰብእናውን አወቃቀር፥ ሊያመለክት የማኅበረሰቡንም ምንነት ሊያሳይ የቻለ ይመስለኛል። እርግጥ፥ ከጽሑፉ ውስጥ እነዚህን ቁምነገሮች ሥርዓት ባለው መልክ አበጥሮ ማውጣት የልዩ ልዩ የዕውቀት ዘርፎች ባለሙያዎች ፈንታ ነው። በጽሑፉ ውስጥ በመደጋገማቸው ምክንያት አፍጥጠው የሚወጡ ቁምነገሮች ሲኖሩ፥ እነዚህ የዘመኑ አሻራ ይሁኑ አይሁኑ ማስረጃዎችን እያጠናቀሩ ያለ ብዙ ድካም አንዳንድ መላ ምት መሰንዘር ደግሞ የንቁ አንባብያንም ፈንታ ይሆናል።
መጽሐፉ ስለ ዘመኑ ግለሰቦች የአካል ብቃትና ጥንካሬ፥ የመንፈስ ጽናት፥ እልህ፥ ወኔ፥ ትዕግስት፥ ብልሃት፥ ፍቅርና ጸብ፥ መተሳሰብ ወዘተ. በመገረም ጭምር እንዳስብ አድርጎኛል። ትረካው ስለሚኪያሄድባቸው ልዩ ልዩ አካባቢዎች (ጫካ፥ ወንዝና ተራራ፥ ከብቶችና አራዊት ወዘተ.) የሚቀርቡትን ገለጻዎች ዛሬ ስለሀገራችን እና ስለዓለማችን ከሚነገረው ጋር እያነጻጸርኩ ስለ ሰው ልጅ የወደፊት ዕጣ እንዳሰላስል የተገደድኩባቸው ጊዜያት ጥቂት አይደሉም። በወቅቱ ይመረቱ የነበሩትን የሰብል ዓይነቶች ገልጸው፥ እነዚህን ከገበሬው ይነጥቁ የነበሩትን የሰማይ አእዋፍና አውሬዎች በስም ዘርዝረው፥ በቂ የእርሻ መሬት ባለመኖሩ ባለርስትና ተጋዥ የሚደርስባቸውን ልፋትና ይኖሩት የነበረውን ዝቅተኛ ኑሮ መጽሐፍ ቅዱስን ጠቅሰው ሲያዝኑ ዘመኔን እያሰብኩ እኔም አዝኛለሁ። የመልክአ ምድር እና የሥነ ምኅዳር ተማራማሪዎች ከእንደነዚህ ዓይነት መጻሕፍት (የየዘመኑን ልብ ወለዶችና ሌሎች መጻሕፍት ጨምሮ) ስላለፈው ዘመን የተለያዩ ሐሳቦችን ሊቀስሙ እንደሚችሉ ተገንዝቢያለሁ። ሌላው ቢቀር በሙያቸው ለሚያደርጓቸው ምርምሮች አንዳንድ ፍንጮች ያገኛሉ የሚል ግምት አለኝ።
በማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ ስላሉ፥ ነዋሪዎቹን እጅ ለእጅ፥ ልብ ለልብ ስላያያዙ እሴቶችም የተገነዘብኩት ብዙ አለ። የትውልድ ስሞች፥ ሐረጎችና ዘርፎች ዝርዝር ለእንደኔ ዓይነቱ የሹሮሜዳ (የአዲስ አበባ) ልጅ “ኦሪት ዘፍጥረት”ን ያስታውሳሉ። አፈ-ታሪክ (ፎክሎር) በጥንቃቄ ካልተመረመረ ታሪክን እንዴት ሊያዛባ እንደሚችል ስለ ቅብርያል ዋሻ የጻፉት ጥሩ ምሳሌ ነው። ስለዚህ ጉዳይ ሲጽፉ፥ “የዋሻው ስም ቅብርያል የተባለበት በአጼ ሱስንዮስ ጊዜ ቅብርያል የተባለ ሰው ዋሻውን ምሽግ አድርጎ ከነጓዙ ተቀምጦበት ስለነበረ ነው። የበደበጅ ባላገር ግን ታሪኩ ጠፍቶበት፥ ቅብርያል የተባለ ቀይ ዘንዶ ነበረበት አሉ፥ እያለ በመላ ሲያወራ ሰምቻለሁ” (ገጽ 17፥ አጽንኦት የኔ) ይሉና የታሪክ ማስረጃቸውን ይጠቅሳሉ (ገጽ 17)። ስለ አተራረክ ስልታቸው ሳወሳ የቅብርያልን ጉዳይ እመለስበታለሁ። አሁን ግን፥ ለአፈ-ታሪክ ጥናት የሚረዳ ሌላ ምሳሌ ላክል።
የመርስዔ ኀዘን የእናታቸው አባት አቶ ምናጣ ይባላሉ። “ክፉ ቀን” በመባል በሚታወቀው የችግርና የረሃብ ወቅት ለወገኖቻቸው ስላደረጉት እርዳታ ለማመስገን “በምናጣ፥ ወጣሁ ስቀናጣ” (ገጽ 51) ተብሎ ተገጠመላቸው። ይህን ግጥም ሌጣውን ባገኘው ምን ማለት እንደሆነ በቀላሉ አልረዳም ነበር። “ምናጣ” ራሱ የሰው ስም መሆኑን ስለማላውቅ የአማርኛ ቅኔን አንድ መንገድ ተከትዬ ባነበብኩበት ቅጽበት ያልሆነ ፍች ልሰጠው እችል ነበር። እንዲህ ከታሪኩ ጋር ስለቀረበ ግን ከብዙ ድካም አድኖኛል። በተመሳሳይ መንገድ፥ ከነአውዳቸው የቀረቡ ሌሎች ቁም ነገሮች በመጽሐፉ ውስጥ አሉ።
ትዝታዬ. . .ን ሳነብ፥ ይገናኛሉ ብዬ የማላስባቸው ነገሮች ተገናኝተው
በማግኘቴ ካድናቆት ጋር የቀሰምኳቸው ቁምነገሮችም አሉ። አጠር ያለ ምሳሌ በጥያቄ አጅቤ ላቅርብ። የማርያም መግደላዊት ቤተ ክርስቲያን በሐ ላይ በመሠራቱ ብዙው የእምቧጮ ሰው ቤተ ክርስቲያኑን ተከትሎ መኖርያውን ወደ በሐ እንዳዞረ መርስዔ ኀዘን ባይጽፉት በምን ይታወቅ ነበር? ዛሬ በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች ይህንን ታሪክ ያውቁ ይሆን? ካላወቁ፥ ያካባቢውን ሕዝብ የአሰፋፈር ታሪክ የሚያጠኑ ሰዎች አንድ የአሰፋፈር ምክንያት አመለከታቸው ማለት አይደለም? በተጨማሪም፥ አንዳንድ በመሠረቱ ያልተለወጡ ነገሮችን በትዝብት አስተውያለሁ። ለምሳሌ፥ ዛሬ የራስ መኰንን ድልድይ የሚባለው ለመጀመሪያ ጊዜ የዛሬ 105 ዓመት ገደማ በኖራና በግንብ ሲሠራ “ሕዝብ ሁሉ እንደ ብርቅ ይመለከተው ነበር” (ገጽ 34) ብለው ሲጽፉ፥ ከብቦት የነበረውን ሰው ብዛት ገምቼ፥ “ዛሬስ ምን ያህል ተለውጠናል?” ብዬ ጠይቄ፥ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ የምላቸውን አውጥቼ አውርጄም፥ ነገሩ እስካሁን ይከነክነኛል፥ አንዳንዴም ያሳፍር ያሳዝነኛል።
ከዚህ በላይ የጠቃቀስኳቸውን የሚመስሉ፥ በዕለታዊ ኑሮ ውስጥ እየተነገሩና እየተገበሩ ሳይመዘገቡ የቆዩ፥ ስለራሳችን እንድንመራመር የሚረዱ ብዙ ቁም ነገሮች በመጽሐፉ ውስጥ አሉ። መዛግብትን፥ ብራናዎችን፥ እና የታተሙ ጽሑፎችን መሠረት አድርጎ ያንድን ሀገር ታሪክ ጽፎ የማሳተም ልምድ ስለገነነ በቃል የሚነገረው፥ በአካል የሚተወነው እና በቁሳቁስ የሚተረከው ተንቆ ቆይቷል። ሰሚ ያጡ የማኅበራዊ ታሪክ ድምጾችም (“መዝገቦች” ልንላቸው እንችላለን) በየአጥቢያው፥ በየመንደሩ፥ በየተራራውና በየሜዳው እያስገመገሙ ኖረዋል፥ ዛሬም እየኖሩ ነው። ስለዚህም ነው፥ የመርስዔ ኀዘን መጻሕፍት ለአንባብያን፥ በተለይም ለወጣቱ ትውልድ ትምህርትን፥ ለተመራማሪዎች መነቃቃትን፥ ለባህል የመስክ ሠራተኞች ደግሞ ትጋትን ይቸራሉ ብዬ ተስፋ የማደርገው።
ትዝታዬ. . . ስለ መርስዔ ኀዘን ልጅነት፥ ጨዋታ፥ እልህ፥ ስለደረሰባቸው ቅጣት፥ በተለይ ደግሞ ስለተከታተሉት ትምህርትና በሥራ ዓለም ስላጋጠማቸው ውጣ ውረድ በብዛት ይተርካል። በአካባቢው እምነት መሠረት ወደ ፊደል ቆጠራ በአራት ዓመት ከአራት ወራቸው ሲገቡ፥ የደብተራ እንደብልሃቱ አለንጋ የማስተማሪያ መሣሪያ ሆኖ ይጠብቃቸዋል። ትምህርት ቤት መሄድ ይጠላሉ። ቤተሰብ ግን አሁንም በድብደባ እንዲሄዱ ሲያስገድዳቸው “በበደበጅ ገደል ዢው ብዬ እገባለሁ. . .” (ገጽ 25) እያሉ ለጓደኞቻቸው ማጫወት ይጀምራሉ። በኋላ ግን ያመርሩና እናታቸው ወዳሉበት ወደ መስቀለሶስ ይኮበልላሉ። ከዚያም ወደ አክስታቸው ወደ እምዬ በሰሙ ዘንድ ይሄዱና፥ “ከዚህ ቀን ጀምሮ ትምህርት ቀረልኝና ሥራዬ ጨዋታ ብቻ ሆነ” (ገጽ 28) ሲሉ በደስታ ይናገራሉ። አባታቸው ዘንድ እንጦጦ ከተመለሱም በኋላ ልዩ ልዩ የገበታ ሥርዓት (ለምሳሌ “ድምጽ ሳያሰሙና ሳያጮሁ ማላመጥ”) ሲማሩ የተሳሳቱ እንደሆነ ስሕተታቸው የሚነገራቸው በኩርኩምና በቁንጥጫ ነበር። አለቃ ወልደ ቂርቆስ ተማሪዎቻቸውን የሚቀጡበት አለንጋ “በላዔ ሰብእ“ (ገጽ 44) ይባል እንደነበረ ይነግሩንና ባላጠፉት ጥፋት በዚሁ አለንጋ ተጠብጥበው እንደነበርም ይተርካሉ (ገጽ 54)። ዝርዝሩ ብዙ ነው። የሶሲዎሎጂና የሥነ ልቡና ባለሙያዎች መጽሐፉን በጥሞና ከዳር እስከ ዳር ወጥተው ቢመረምሩ ስለ ቤተሰብ፥ ስለ ልጅ አስተዳደግ፥ ስለ ልጅነት ጨዋታ፥ ተንኮል፥ አመጽ እና ከእነዚህ ጋር ስለሚዛመዱ ሌሎች ጉዳዮች ለምርምር የሚጠቅም ብዙ ሐሳብ እንደሚያገኙ ጥርጥር የለኝም። አንባብያንም፥ ብዙ ጊዜ በወላጆችና በባህሉ ዓይን ከሚተረኩት የልጆች ልምዶች ወጣ ተብሎ በሕፃናቱና በልጆቹ ዓይን እየታዩ የሚቀርቡ ትረካዎችን ያነብባሉ። በሌላ ዘመንና ቦታ ተፈጽመው ያልተጻፉትን ልምዶቻቸውን እያስታወሱ ፈገግ ይላሉ። ወይም ደግሞ አልፈው የመጡትን፥ በየምክንያቱ በውስጣቸው ያንቀላፋውን ልጅነታቸውን እየቀሰቀሱ እንደኔ በትዝታ ይኮረኮራሉ፥ በለኆሳስ ይፍነከነካሉ።
የትምህርት ባለሙያዎች ደግሞ ስለ ጥንቱ የግዕዝ ትምህርት ቤት አኪያሄድ፥ በየደረጃው ስለሚሰጡት የትምህርት ዓይነቶች፤ የትምህርት ዓይነቶቹ ስለሚጠይቁት ችሎታ፥ ትዕግስትና ትጋት፥ ተማሪው በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ሲያልፍ በየደረጃው ስለሚገነመው ሰብእና፥ በመምህራኑና በተማሪዎች እንዲሁም በሊቃውንቱ መሀከል ስለነበሩ ግንኙነቶች ወዘተ. ልኩ በቀላሉ የማይሰፈር ዕውቀት ያገኛሉ። ሳናውቀው በስሕተት፥ በድፍረት፥ በአጉል ትዕቢት፥ በንቀትና በጭፍኑ ያንኪያኬስነውን የቃል ትምህርትን ጥቅምና ጉዳት “ምሁራን” የምንባለው ሁሉ እንደገና መመርመር እንዳለብን የሚያሳስቡ ብዙ ቁም ነገሮች በሁለቱ የመርስዔ ኀዘን መጻሕፍት ውስጥ አሉ። አንድ ምሳሌ ከትዝታዬ. . . ልጥቀስ።
የአረጋዊ መንፈሳዊ መጽሐፍ በመባል የሚታወቅ፥ መምህር አካለ ወልድ ከመቱ አብሯቸው ይመታል የሚል ሥጋት ያሳደረ መጽሐፍ ነው። ሥጋቱ የመጣው የዚህ መጽሐፍ የትርጓሜ ትምህርት በቃል ይተላለፍ ስለነበረ ነው። ልዑል አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ ለመምህር አካለ ወልድ ደብዳቤ ጽፈው ንመቡን ከነትርጓሜው እንዲጽፉ ጠይቀዋቸው ነበር። ነገር ግን ጀምረው ሳይጨርሱት ኅዳር 9 ቀን 1912 ዓ.ም. ስላረፉ ሥራውን ተፍጻሜ የሚያደርስ ሰው ሲፈለግ መምህር ደስታ ይገኛሉ። ከዚህ በታች የምጠቅሰው መምህር ደስታ የትርጓሜው ትምህርት ከማን፥ ለማን እየተላለፈ እርሳቸው ዘንድ እንደደረሰ ለመርስዔ ኀዘን የነገሯቸውን ነው።
ጊዮርጊስ ሶርያዊ ለድምሆይ ዘምሥሐለ ማርያም አስተማረ
ድምሆይ ዘምሥሐለ ማርያም ለጥበበ ክርስቶስ አስተማረ
ጥበበ ክርስቶስ ለሐዋርያነ ክርስቶስ አስተማረ
ሐዋርያነ ክርስቶስ ለሊቀ ካህናት ወልደ ዮና አስተማረ
ሊቀ ካህናት ወልደ ዮና ለእጨጌ በትረ ጊዮርጊስ አስተማረ
እጨጌ በትረ ጊዮርጊስ ለዓቃቤ ሰዓት አብራንዮስ አስተማሩ
ዓቃቤ ሰዓት አብራንዮስ ለመንፈቆ ወልደ ሃይማኖት አስተማሩ
መንፈቆ ወልደ ሃይማኖት ለመምህር ሙሴ አስተማሩ
መምህር ሙሴ ለመምህር ሐሊብ አስተማሩ
መምህር ሐሊብ ለመምህር ሀብቱ አስተማሩ
መምህር ሀብቱ ለመምህር አካለ ወልድ አስተማሩ
መምህር አካለ ወልድ ለመምህር ደስታ አስተማሩ (ገጽ 137)
በአጼ ገላውዴዎስ ዘመን፥ ጊዮርጊስ ሶርያዊ ለድምሆይ ዘምሥሐለ ማርያም ካስተማረበት ጊዜ ጀምሮ መርስዔ ኀዘን ተምረው በ1912 ዓ.ም. እስከጽፉት ድረስ የአረጋዊ መንፈሳዊ መጽሐፍ የትርጓሜ መጽሐፍ ትምህርት እየተሰጠ ከዘመን ዘመን የተላለፈው በቃል ጥናት ብቻ ነበር። ትርጓሜውን በማስተላለፍ ሥራ የተካፈሉት ሊቃውንት መርስዔ ኀዘንን ጨምሮ 14 ነበሩ። መጽሐፉ በ1922፥ ድሬዳዋ በነበረው፥ ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኰንን ማተሚያ ቤት መታተሙን አቶ አምኃ በግርጌ ማስታወሻ ገልጸዋል። ከዚህ ምን መማር እንደሚገባ ለአንባብያንና ለተማሩ ኢትዮጵያውያን እተወዋለሁ።
ስለ ትዝታዬ. . . መጥቀስ ያለብኝ ሌላው ነጥብ የአተራረክ ስልታቸውን ይመለከታል። ማስተዋወቂያዬ እየረዘመ ስለመጣ በተቻለ መጠን አሳጥሬ ልናገር። የአተራረክ ስልታቸው ሁለቱን መጻሕፍት ይዞ፥ ሌሎች ሥራዎቻቸውንም ጨምሮ ራሱን ችሎ የሚጠና ነው። ከዚህ ቀጥዬ ለአብነት ያህል የማነሳው ግን ግለ-ታሪካቸውን ለመጻፍ ለሚያስቡ ሁሉ መልካም ማስታወሻ ይሆናል የምለው ነው። ይኸውም አንድ ታሪክ እየተረኩ፥ በመሃል የሚመጣ ሌላ ትረካን ያለ እክል የመቀጠል ክሂላቸውን የሚመለከት ነው። እንዲህ ነው።
ቀደም ብዬ ያነሳሁት፥ የኦርቶዶክሳዊው ግብድዊ የቅብርያል ታሪክ (ገጽ 17- 18) የመርስዔ ኀዘን ታሪክ ዓቢይ አካል አይደለም። ቅብርያል የሚባለውን ዋሻ ያነሱና ስለዋሻው ስያሜ አገሬው የሚለውንና በታሪክ ድርሳን የተመዘገበውን ይነግሩናል። ከዚያ በኋላ፥ “ቅብርያልን ካነሣሁ ዘንድ ስለ ታሪኩ ጥቂት መግለጫ መስጠት ይገባኛል” በሚል ማስታወሻ በትረካቸው ውስጥ ስለሚመጣ ሌላ ተረክ (narrative) አንባቢውን አሳስበው ይቀጥላሉ። የቅብርያልን ታሪክ ሲጨርሱ ደግሞ፥ “እንግዲህ ወደ ታሪኬ እመለሳለሁ” ብለው ወደ ዋናው ትረካ ይመለሳሉ። ከዋናው የታሪክ መስመር ሲወጡና ጣልቃ የገባውን ታሪክ ሲጨርሱ መናገራቸው አንባቢ በሥርዋጽ ትረካው እንዳይደናቀፍ፥ ዓቢይ ትረካውም ከቆመበት ተነሥቶ ኮለል ብሎ እንዲፈስ አድርጓል። ይህ የመልካም ተራኪ፥ የልባም አውጊ አንድ መለዮ ይመስለኛል። የምዕራፍ 2 የመጨረሻ ዓረፍተ ነገርም በተከታዩ ምዕራፍ የሚመጣውን ሌላ ሥርዋጽ ትረካ የሚያመለክት ነው። በምዕራፍ ሦስት ሰለ ወላጆቻቸው ከጻፉ በኋላ የመጨረሻው ዓረፍተ ነገር “እነሆ የወላጆቼን ዜና ባጭሩ ጽፌ አቆምሁ” ይሉና በምዕራፍ አራት ውስጥ የራሳቸውን ታሪክ ያወሳሉ። ሌሎች የትረካ ዘዴዎችም አሉ። የሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎች ትረካውን፥ ዓረፍተ ነገሮቹን፥ ቃላቱንና ሐረጎቹን በመመርመር ጸሐፊው ሐሳባቸውን ለአንባቢም ይባል ለትውልድ ለማስተላለፍ የተጠቀሙባቸውን ስልቶች እንዲያጠኑ እመክራለሁ። ያንድን ቁም ነገር ታሪካዊነትና ቀጣይነት (continuity) አንባቢ እንዳይስት ለማድረግ በአጽንኦት ስልት የሚጠቀሙባቸውን ጊዜያት፥ አንባቢ ትረካውን በትኩረትና በትጋት እንዲከታተል የሚያደርጉባቸውን መንገዶች፥ አንባቢ የሚያስተላልፉትን መልእክት እንዳስተላለፉለት እንዲቀበላቸው ሲፈልጉ የሚገለገሉባቸውን ተደጋጋሚ ስልቶች፥ አንባቢን፥ የሰዎችን ሐሳብና ስሜት፥ የተመለከቷቸውን አንዳንድ ድርጊቶች የሚገልጹባቸውን ብልሃቶች እና ሌሎች ቴክኒካዊ ጉዳዮች ፈልፍለው ሊያወጡ፥ ስለ መርስዔ ኀዘን የአጻጻፍ ዘዬ/ዘዬዎች ሊተውሩ ይችላሉ የሚል አስተያየት አለኝ። ከፍ ብዬ ባቀረብኩት ምክንያት የትረካን ጉዳይ በዚሁ አበቃለሁ።
በአፈ-ታሪክ ምርምር ክቡር ስፍራ ካላቸው ምሁራን አንዱ ያን ቫንሲና (Jan Vansina) ትውፊት እንደ ታሪክ (Oral Tradition as History) በተባለው፥ የዛሬ 25 ዓመት ገደማ በታተመው መጽሐፉ፥ አንድ መረጃ ወይም መልእክት ከየት-ከየት እንደሚገኝ፥ እንዴት ከሰው ወደ ሰው፥ ከቦታ ወደ ቦታ፥ ከዘመን ዘመን እንደሚተላለፍ፥ እንዴት እንደሚሰበሰብ፥ እንደሚደራጅ እና እንደሚጠና በሰፊው ያትታል። አንዱ መልእክት ከአንዱ ወደ ሌላው በሹክሹክታ የሚተላለፍ የቅርብ ጊዜ ዜና ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ አንድ ግለሰብ ስለራሱ ምኞት፥ ትናንት ሌሊት በሕልሙ ስላየው ነገር፥ ስላጋጠመው ራዕይ፥ የሚያወራው ወሬ በሹክሹክታ ሊራባ ይችላል። በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚነገሩ ትንቢቶችም መልካቸውን እየለዋወጡ በነዋሪዎቹ መሀከል ይተላለፋሉ። በትዝታ መልክ የሚተረኩ፥ ስለአንዳንድ የቦታ ስያሜዎች ምንጭ እና ስለነገራት አመጣጥ የሚነገሩም አሉ። በግጥም፥ በተረት፥ በምሳሌያዊ ንግግር መልክ የሚቀርቡም አሉ። ሌላው መልእክት፥ አንድ ድርጊት ሲፈጸም አይቶ፥ ያንን ያየውን እና የሰማውን ጉዳይ፥ የአድማጮቹን ማንነት፥ ያለበትን ቦታና ሁኔታ፥ እና ጊዜውን እየመዘነ አንድ የዓይን ምስክር የሚያቀርበው ቃልም ሊሆን ይችላል። ዝርዘሩ ብዙ ነው። ባጭሩ፥ እነዚህ እና እነዚህን የመሳሰሉ መልእክቶች ሁሉ የአንድ ግለሰብ፥ የአንድ መንደር፥ ወይም ሀገር ታሪክ ሲጠና የሚያበረክቱት ነገር አለ። ስለዚህም የሚሰበሰቡበት፥ የሚጣሩበት፥ የሚጠናቀሩበት እና ተደራጅተው የሚቀርቡበት መንገድ-መንገድ አለ። እነዚህን መንገዶች መሠረት አድርጎ ታሪክ መጻፍ ቀላል ሥራ አይደለም። በውትድርና ቋንቋ የግለ-ታሪክና የአፈ-ታሪክ ምርምር ፈንጂ የሚበዛበት መስክ ስለሆነ እያዩ፥ እያስተዋሉ፥ እየመረመሩ፥ በጥንቃቄ የሚጓዙበት መስክ ነው ማለት ማጋነን አይሆንም። ተጠንቅቆም ሁሉን ባይሆን ብዙውን የሚያረካ ሥራ ሠርቶ ማቅረብ ከተአምር የሚቈጠር ነው ማለት ይቻላል።
ዛሬ፥ ከዚህ በላይ የጠቃቀስኳቸውን ዓይነት የምርምር ዘዴዎችና ትውሮች ይዞ፥ የግለሰብ ታሪክ የሚያጠና ተመራማሪ ከመረጃ አቀመዮች በኢንተርቪው ከሰበሰበው መረጃ አብዛኛው አስተማማኝ የዓይን ምስክር መረጃ ከሆነለት ለሥራው ደኅንነት አንድ መነሻ ፍንጭ አገኘ ማለት ስለሆነ በደስታ ይቦርቃል። መርስዔ ኀዘን ባለፉት ኢ ገደማ ዓመታት እየዳበሩ ከመጡት የቃል ታሪክ ጥናት ዘዴዎችና ትውሮች (methods and theories) ጋር ሳይተዋወቁ በእኔ አስተያየት፥ በተግባር ግን ጥቂት የማይባሉትን ፈጽመዋል። ያዩትን “አየሁ!”፥ የሰሙትን “ሰማሁ!” እያሉ ነው በየቦታው የተረኩልን። በአፈ-ታሪክ፥ በግለ-ታሪክ ወይም በፎክሎር ተመራማሪ ቢጠየቁ የሚናገሩትን በወግ፥ በጨዋታ መልክ ራሳቸው ያቀረቡልን መስሎ ነው የተሰማኝ። ሁለቱንም መጽሐፎች ሳነብ፥ የሚተርኩልኝን የተከታተልኩት በዓይነ-ሕሊናዬ እያየሁ፥ በእዝነ-ኅሊናዬ እየሰማሁና እያደመጥኩ የነበረ ይመስለኛል። ይህ ደግሞ ከተመራማሪው በተዘዋዋሪ አገኝ የነበረውን ከርሳቸው በቀጥታ ከነወዙ እንዳገኝ አድርጎኛል። ካካበቱት ልምድና ዕውቀት፥ የ20ኛውን ክፍለ ዘመን መባቻ የሚያጠኑ ተመራማሪዎች፥ እንዲህ እቅጭ-እቅጩን፥ ግልጽ በሆነ ቋንቋ፥ ቁልጭ አድርገው ያቀረቡ፥ ወደፊትም የሚያቀርቡ ኢትዮጵያውያን ስንት ይሆኑ? ቊጥራቸው እንዲበዛ እመኛለሁ።
አቶ አምኃ ትዝታዬ. . .ን አንብቤ ማስተዋወቂያ እንድጽፍ ስለጠየቀኝ ስለ
እኚህ ታላቅ ሰው መጻሕፍት አንዳንድ ትኁት አስተያየቶች ጭሬያለሁ። በዚህ የተነሣ፥ አልፎ አልፎ ስሜ ከእርሳቸው ሥራዎች ጋር፥ ፈቀድኩም አልፈቀድኩም፥ መነሣቱ አይቀርም። ለዚህ መብቃት መታደል ነው። አቶ አምኃን ከልብ አመሰግነዋለሁ።
የአባቱን መጻሕፍት በጥንቃቄ አዘጋጅቶ፥ ለአዘጋጁ በጣም አድካሚ ለአንባቢና ለተመራማሪ ግን እጅግ ጠቃሚ የሆኑትን ግርጌ ማስታወሻዎች፥ አባሪዎችና መጠቁም (ለindex ፕሮፌሰር ጌታቸው የሰጡት መጠሪያ ነው) አደራጅቶ ስላሳተመ በድጋሚ አመሰግነዋለሁ። አንባብያንም የመርስዔ ኀዘንን መጻሕፍት እያነበቡ እንዲደሰቱ፥ እንዲገረሙ፥ እንዲቆዝሙ፥ እና እንዲማሩ በትኅትና እጋብዛለሁ። እመው እና አበውም፥ በሕይወት ዘመናቸው ያዩትንና የሰሙትን እንዲጽፉልን፥ ወይም ደግሞ በዘመናዊዎቹ የድምጽና የምስል መቅረጫዎች እንዲያቀርቡልን አደራ እላለሁ!
ፈቃደ አዘዘ
በ “የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ክፍለ ትምህርት“፥ መምህር
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
መጋቢት 8 ቀን 2001 ዓ.ም.